በዞኑ የትምህርት ጥራት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከመንግስት ጎን በመሆን እያደረጉት ያለው ንቁ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።


በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ በብሩህ ተስፋ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ ድርጅት በማህበረሰቡና በወረዳው መንግስት ትብብር በ20 ሚሊየን ብር የተገነባው የፈረስ ጉራ የሻለቃ ሱልጣን ሼህ ኢሳ የ1ኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለመማር ማስተማር ክፍት ሆነ።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በፕሮግራሙ ተገኝተው እንዳሉት በዞናችን ብሎም በሀገራችን ደረጃቸው የጠበቁ፣ሙሉ ግብአት ያሟሉ፣በሳይንሳዊ መንገድ የተመሩ ትምህርት ቤቶች ባለ መኖራቸው የትምህርት ውጤት ስብራት መንስኤ ሆነዋል።

የዞኑ መንግስት እንደሀገር የገጠመው የትምህርት ስብራት ለመጠገን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር፣ከማህበረሰቡ፣ ከባለሀብቱ፣ከሙህራን እና ከአጋር ድርጅቶች ንቅናቄ ተፈጥሮ ሀብት መሰብሰቡ ተናግሯል።

በዚህም በርካታ ትምህርት ቤቶች መገንባትና በመጠገን የተቻለ ሲሆን ለብዙ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ቁሳቁስ የማሟላት ስራ መሰራቱ ገልጸዋል።

አቶ አበራ አክለውም የዞናችን የትምህርት ውጤትና ጥራት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ድርጅቱ ትምህርት ቤት በመገንባት፣መምህራን በማሰልጠን፣ጎበዝ ተማሪዎችን በመሸለም እና ግብአት በማሟላት የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

አክለውም በዞኑ የትምህርት ጥራት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከመንግስት ጎን በመሆን እያደረጉት ያለው ንቁ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብስራት ገብሩ እንደገለፁት በወረዳው በ37 የመጀመሪያና ደረጃና በ7 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመደበኛ የትምህርት ዘርፍ ከ18 ሺ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸው እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ከእነዚህም የብሩህ ተስፋ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለፈረስ ጉራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ትምህርት ቤቱ መስራቱ ለትውልድ የሚተላለፍ ተግባር መሆኑ ምስጋናቸው አቅርበዋል።

ይህ ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ተማሪዎች በምርምር፣በፈጠራ፣በጥበብና በውጤት የሚበለጽጉበት ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ ብስራት ተማሪዎቹም በርትተው ተምረው በቀጣይ ደግሞ መሰል የበጎ አድራጎት ስራ እንዲሰሩ ከአሁንኑ ጠንክረው እንዲማሩ መክረዋል።

ትምህርት ቤቱ በዛሬ እለት በፈረስ ጉራና በወረዳችን ህዝብ ብሎም በዞናችን መልካም አራያነት ስም በሚታወቁት የሻለቃ ሱልጣን ሼህ ኢሳ ስም “በፈረስ ጉራ የሻለቃ ሱልጣን ሼህ ኢሳ 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” መታሰቢያነት የተሰየመ ሲሆን በመላው ቤተሰቦቻቸው ድጋፍና አጋርነት የሚተዳደር እንደሚሆን አስታውቀዋል።

በጀርመን ሀገር የብሩህ ተስፋ የገጠራማው ኢትዮጵያ የልማት ድርጅት ኃላፊ አቶ ብዙ አየሁ ገረመው ዛሬ የተመረቀው የፈረስ ጉራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 5 ብሎኮች እና 20 የመማሪያ ክፍሎች የተገነባ ሲሆን ፣የአስተዳደር ቢሮዎች፣ኮምፒተሮች፣ቤተ መጽሀፍት፣ቤተ ሙከራና የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁሶች ተሟልተውለት ለተማሪዎች ለመማር ማስተማር ምቹ ተደርጓል።

ቢሆንም በዞኑ ያሉ የአካባቢ ተወላጆች በየ አካባቢያቸው መሰል አይነት የትምህርት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲሰሩ የመከሩት አቶ ብዙ አየሁ ፕሶጀክቱ በሌልች ወረዳዎችም መሰል ስራዎች እየሰራ ሲሆን እያደረገ ያለው ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ጌታሰው ታምሩ በበኩላቸው ተማሪዎች ደረጃውን በጠበቀ ትምህርት ቤት መማራቸው የመማር ፍላጎታቸው እንዲዳብር ከማድረጉ በተጨማሪ የትምህርት ውጤት መሻሻል ከፍተኛ ሚና አለው ነው ያሉት።

ትምህርት ቤቱ በአሁን ሰአት እስከ 4መቶ የሚደርሱ ተማሪዎች ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን በቀጣይም በትምህርት ቤቱ ሙሉ ቁሳቁስ ለማሟላት የመማሪያ ቁሳቁስ እና ተጨማሪ መምህራን ይፈልጋል ብለዋል።

በትምህርት ቤቱ ያገኘናቸው ተማሪዎች እንዳሉት ትምህርት ቤቱ ከዚህ በፊት እጅግ የተጎሳቆለ እና ለመማር ማስተማር ምንም የማይመች የነበረ በመሆኑ ብዙ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተፈናቅለዋል ሲሉ አስታውሰዋል።

እነሱ ግን በደንጋይ ቁጭ ብለው እና አቧራውን በየ ሳምንቱ እበት እየቀቡ እየተማሩበት እንደነበር አስገንዝበዋል።

ዛሬ ትምህርት ቤቱ በጥሩ ሁኔታ ተሰርቶ ማየቱ እጅግ ተደስተናል ያሉ ሲሆን በቀጣይ በትምህርታችን በርትተን ተምረን ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንሰራለን ብለዋል።

በመጨረሻም ለትምህርት ቤቱ ግንባታ አስተዋጾ ላደረጉ ተቋማትና አካላት ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *