በዞኑ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የለባቸው የክህሎት ክፍተቶች ላይ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ገለጸ።

ብሪጅ ፈርስት ፕሮግራም ከጉራጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ጋር በመተባበር በአደራ ኮንሰልታንሲ አስፈጻሚነት በዞኑ የሚገኙ ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በንግድ ልማትና አገልግሎት ላይ ለመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች ለ3 ተከታታይ ቀናት በወልቂጤ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ።

ሁለተኛው ዙር ስልጠና በቀጣይ በአረቅጥና በጉንችሬ ከተማ አስተዳደር እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

የጉራጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ያሲን በወቅቱ እንዳሉት የስልጠናው አላማ የኢንተርፕራይዞችን የክህሎትና የአመለካከት ክፍተትን በመለየት አጠቃላይ በክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራሞች ላይ አቅም ለማጎልበት ያለመ ነው።

መምሪያው ከብሪጅስ ፈርስት ኮንሰልታንሲ ፕሮግራም በገባው የውል ስምምነት መሰረት በዞኑ በሁለቱም ዙር ለ4መቶ ኢንተርፕራይዞች ወይም 1ሺህ 5መቶ ለሚሆኑ አንቀሳቃሽ በሴት ብቻ ለተደራጁ ሴት ኢንተርፕራይዞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በወልቂጤ ከተማና በአገና ከተማ አስተዳደር መሰጠቱን ጠቅሰው በቀጣይም በአረቅጥና በጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛው ዙር ስልጠና እንደሚሰጥም አመላክተዋል።

መምሪያውና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በየጊዜው በስራ ዕድል ፈጠራ አመለካከትና አስተሳሰብ ብሎም ውጤታማነት ላይ መሰረት ያደረጉ ስልጠናዎች በየጊዜው እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ሙራድ መሰል ስልጠናዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ ለማድረግ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የመስሪያና መሸጫ ቦታ፣ የማሽኖች፣ የክህሎት እና የፋይናንስና ብድር አቅርቦት ችግር መኖሩን ጠቁመው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የፋይናንስና የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ብሎም ባንኮች የፋይናስ የብድር አቅርቦት እንዲያግዙ የተጀማመሩ ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ከሰልጣኝ ኢንተርፕራይዞችም አሁን ላይ ያለው የሂሳብ አያያዝ እንዲያሻሽሉ፣ በዘርፉ ውጤታማ በመሆን ብቁና ከሌሎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የንግድ ንድፈ ሀሳብ ክህሎታቸው በማሻሻል በቀጣይ ውጤታማ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም በዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የፕሮግራሙ ፈፃሚና የአደራ ኮንሰልታንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ መኑር ባዴ በበኩላቸው ኢንተርኘራይዞች ብቁ ፣ አምራችና፣ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆኑ ስልጠናው በተገቢው መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

ስልጠናው ከሰጡት መካከል አሰልጣኝ ተፈራ በየነ እንዳሉት ሰልጣኞች በስልጠናው ወቅት ያገኙትን ግንዛቤ ተጠቅመው በስራቸው ላሉ አባላት ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ስልጠናውም በንግድ ንድፈ ሀሳብ እቅድ አዘገጃጀትና ምንነት፣ በሂሳብ ገንዘብ አያያዝ፣ በገበያ ትስስር፣ ሞዴል የሆነ ምርታማነት፣ ጥራትና ተወዳዳሪ የሆነ የምርት አቅርቦት እና ሌሎችም ላይ ስልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።

ሰልጣኞች እንደገለጹት ስልጠናው ገንቢና ከዚህ በፊት በመዝገብ አያያዝና በሌሎችም የነበረባቸውን የክህሎት ክፍተት እንደሞላላቸው ጠቁመዋል።

በስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ተጠቅመው ለአባሎቻቸው ከማስገንዘብ ባለፈ የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚተጉም ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም በስራቸው ይበልጥ ውጤታማና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰል ስልጠናዎች በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸውም ጠይቀዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *