በዞኑ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙና የፍትህ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር መስራት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2016 በጀት አመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት እቅድ አፈጻጸም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የግምገማ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ሰብለጋ እንደገለጹት በዞኑ ባለፉት 6 ወራት የጸጥታ ችግሮችን እንደነበሩ ገልጸው በዚህም በተሰራው ህግ የማስከበር ስራ አመርቂ ውጤት ተመዝግባል ብለዋል።

በተለይም የግድያ፣ የውንብድና የስርቆትና ሌሎችም በየደረጃው የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ተገቢውን የህግ ምርመራ በማድረግና በማጣራት ለፍርድ ቤት በማቅረብ መዝገቦች ውሳኔ እንዲያገኙ እንደተደረገም ጠቁመዋል።

በዞኑ በየደረጃው የሚስተዋሉ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ህግን መሰረት በማድረግ ተገቢውን ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ ህግ የማስከበር ስራ መሰራቱንም በመግለጽ።

ባለፉት 6ወራት ከ7መቶ በላይ የወንጀል ምርመራ ኬዞችን በማጣራት ለፍርድ ቤት በማቅረብ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ተደርጓል ብለዋል።

እነዚህም የግድያ፣ የውንብድና የዘረፋ፣ ቀላልና ከባድ የስርቆት፣ የሴቶች አስገድዶ የመድፈር፣ የግድያና ሌሎችም ወንጀሎችን መፈጸማቸውን ያነሱት ኃላፊው በእነዚህም ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ውሳኔ የማሰጠት ስራ እንደተሰራም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በየደረጃው ቀላልና ከባድ የተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን በተጠናከረ መንገድ ከፖሊስ ጋር በመናበብ ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን አስረድተዋል።

አቶ ኤልያስ በፍትሐብሄር ዘርፍ ከአፈር ማዳበርያ፣ ከኦሞ መደበኛ ስርጭት፣ ከወጣቶች ብድር ተዘዋዋሪ ፈንድ ጋር ያለአግባብ የተመዘበሩ የመንግስትና የህዝብ ንብረቶችን በክስና በድርድር በሁሉም የህግ ዘርፍ 46ሚሊዮን ብር ማስመለስ ተችሏል ነው ያሉት።

እንደ አቶ ኤሊያስ ገለጻ ከታክስ ኦዲት ጋር በተያዘ፣ ከአፈር ማዳበሪያ፣ ከኦሞ ባንክ መደበኛ ብድር ስርጭት እና ከወጣቶች ብድር ተዘዋዋሪ ፈንድ ጋር ተያይዞ ያልተመለሱና ያደሩ ቀሪ የመንግስት ሀብትና ንብረት የሆኑ የፍትሐብሄር ገንዘቦችን ቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ማስመለስ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በዞኑ የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች በመከላከልና የሚፈጸሙ ወንጀሎች በማረም ህግ የማስከበር ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት የፍትህ ተቋማት የተጣለባቸውን ፍትህን የማስፈን ኃላፊነት በትኩረት መስራት እንዳለባቸውና ለዚህም ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ይገባል።

በተለይም ያለአግባብ የሚመዘበሩ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ለማዳን በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎች አክለውም በእቅድ አፈጻጸም ወቅት በተሻለ መልኩ የተከናወኑ ስራዎችን በማጠናከርና ያልተከናወኑ ተግባራቶችን በመውሰድ በቀጣይ በዘርፉ ውጤታማ ስራ እንደሚሰሩ አመላክተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *