በዞኑ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

ሚያ

መምሪያው ከአጋፔ ሞብሊቲ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በዞኑ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች የዊልቸር ድጋፍ አድርጓል።

የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን እንደገለጹት በዞኑ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውና ተሳታፊነታቸው ለማሳደግ መምሪያው እየሰራ ይገኛል።

እንደ ሀገር ብሎም እንደ ዞን በአካል ጉዳተዳኞች ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ የነበሩ የአመለካከት ችግር እንዲቀረፉ በተሰሩ ስራዎች የተሻለ ለውጥ መኖሩንም አመልክተዋል።

በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የአካል ጉዳተኞች ማህበራት በበጀት፣ በቁሳቁስ የማጠናከር ስራ ከመስራት ባለፈ በቅርቡ ዞናዊ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ጥምረት እንዲመሰረት በማድረግ መብቶቻቸው እንዲያስከብሩና ከማህበረሰቡ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

መምሪያው በባለፉት ወራት ለአካል ጉዳተኞች 63 አዲስ ቤት የመገንባትና 64 የቤት ጥገና ማድረጋቸውን ያነሱት አቶ መኩሪያ ከዚህ ባለፈ አካል ጉዳተኞች በስፖርቱ ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ያሉ አካል ጉዳተኞች ችግር በመንግስት ብቻ የሚቀረፍ ባለመሆኑ በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን ከነዚህም የአጋፔ ሞብሊቲ ኢትዮጵያ በአምና ደረጃ 42 ዊልቸር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በዛሬው እለትም ከወልቂጤ መካነ ኢየሱስ ምዕመናን ጋር በመተባበር መምሪያው ያቀረበው ፕሮፖዛል በመቀበል 40 ዊልቸር ድጋፍ ማድረጉና ይህም በገንዘብ ሲተመን 1ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዞኑ ከ23 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች መኖሩን የገለጹት ኃላፊው ለአካል ጉዳተኞች የሚደረገው ድጋፍ የህሊና እርካታ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪም ዘንድ የሚያስመሰግን ተግባር በመሆኑ እነዚህን ወገኖች ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ደሳለኝ ፈቀደ በበኩላቸው በዞኑ በየአካባቢው አስታዋሽ ያጡ ከቤት ውስጥ ወጥተው ብርሃን እንዲያገኙና ከጎረቤታቸው ጭምር እንዲገናኙ የአጋፔ ሞብሊቲ ኢትዮጵያ ላደረገው የዊልቸር ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም መሰል ስራዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የዞኑ አስተዳደር ድርጅቱ ለሚያደርገው ድጋፍ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመው ድጋፉ የተደረገላቸው አካል ጉዳተኞችም የተሰጣቸው ስጦታ በተገቢው መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአጋፔ ሞብሊቲ መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ሳባ ወልደማርቆስ አጋፔ ሞብሊቲ ኢትዮጵያ መሬት ላይ የመንፏቀቅ ዘመን ያበቃል የሚል አላማ አድርጎ የሚሰራ ድርጅት መሆኑን ገልጸው አካል ጉዳተኞች ከማንም ዜጋ እኩል መሆናቸው ተናግረዋል።

በዞኑ የዊልቸር ድጋፍ ሲያደርጉ ለሁለተኛ ዙር መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሳባ በዛሬው እለት ዊልቸሩ ድርጅቱ ከፍሪ ዊልቸር ሚሽን ከሚባል ድርጅት ያገኙትን ድጋፍ ለዞኑ አካል ጉዳተኞች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው በቀጣይም የሚያደርጉት ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

ዊልቸር ለአካል ጉዳተኛው እግር ጭምር ነው ያሉት መስራችዋ ዊልቸሩ በመጠቀም መማር፣ መነገድ፣ የትኛውም ስራ ከማንም እኩል በመስራት ህይወታቸው እንዲቀይሩበማሰብ ድርጅቱ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የወልቂጤ መካነ ኢየሱስ ማህበረ ምዕመናን መሪ ቄስ አዲሱ አወቀ ቤተክርስቲያኑ በከተማው ብሎም በዞኑ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

አካል ጉዳተኝነት በተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚከሰት በመሆኑ አጋፔ ሞብሊቲ ኢትዮጵያ ከዞኑ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል 40 ዊልቸር ድጋፍ ላደረጉ ለአጋፔ ሞብሊቲ ኢትዮጵያ ምስጋና አቅርበዋል።

የዊልቸር ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አቶ ኤልያስ ሀይሌና ወይዘሮ ሀሚዳ ደገሙ በተደረገላቸው የዊልቸር ድጋፍ ደስታቸው ወደሬለሽ መሆኑን ገልጸው ለተደረገላቸው ድጋፍም አመስግነዋል።

ከዚህ በፊት የዊልቸር ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ይቸገሩ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ የተደረገላቸው ዊልቸር በመጠቀም ትምህርታቸው ለመማርና ስራቸውን ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *