በዞኑ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የበለጠ እንዲነቃቃ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው ከወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር ለቱሪስት አገልገሎት ሰጪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በጆካ ኢኒተርናሽናል ሆቴል ለ2 ቀን ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንደገለፁት ስልጠናው እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የሚሰጠ ሲሆን በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ተቀርፈው ውጤቶች እንዲመጢ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በተለይ የመጸዳጃ ቤት አያያዝ፣የመኝታ ክፍል ንጽህና፣በሆቴሎችና በከተማው የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት ፣ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪና ሌሎች ችግሮች ማስተካከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ወ/ሮ መሰረት አክለውም የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የበለጠ እንዲነቃቃ አገልገሎት ሰጪ ተቋማት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ የገለጹ ሲሆን ሆቴሎች አለባበሳቸው የጉራጌ ብሎም የሀገራችን ባህልና እሴት በሚገልጽ መልኩ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል።

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ ተቋማቸው በሚዲያ ማስተዋወቅ፣ስፖዚየም፣ባዛር፣ወርክ ሾፖችን በማዘጋጀት ውጤታማ እንዲሆኑ መስራት

በሆቴሎች የሚሰሩ ሰራተኞችም በሙያው የሰለጠኑና ሙሉ እውቀት ያላቸው መሆን ያለባቸው ሲሆን ለስልጠናው አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸው አቅርበዋል።

የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ኢኒስቲትዩት ዲን አቶ ኸይሩ አህመዲን በዚህ ወቅት እንዳሉት በዞኑ ከቅርብ አመታት ጀምሮ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ የታየው መነቃቃት አጠናክሮ ለማስቀጠል የኮሌጆች ሚና ከፍተኛ ነው።

ኮሌጁም ዘርፉን ሊያነቃቁ የሚችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመስራት፣በኮሌጁ የሚሰጠው የሆቴልና ቱሪዝም ኮርሶችን በማጠናከርና፣የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራት የበኩሉን እንደሚወጣ ያስገነዘቡት አቶ ኸይሩ ሆቴሎች መስተንግዶዋቸው በዲጂታል እንዲሆኑ የአሰራር ስርአት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የመምሪያው የቱሪስት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቃት ማረጋገጫ ዋና ስራ ሂደት ባለሙያ ወ/ሮ ወይንሸት ሰተቶ በስልጠናው ወቅት እንደተናገሩት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ለመቅረፍና አገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማ ለማድረግ ሴክተር ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አብራርተዋል።

በአግልግሎት ሰጪ ተቋማቶች ችግሮች ሲገጥሙ በማስተማርና በመወያየት መሆን አለበት ያሉት ወ/ሮ ወይንሸት ወደ ዞኑ የሚገቡ ቱሪስቶች በተቋማቶቹ ተደስተው እንዲሄዱ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በስልጠናው የተሳተፉ አካላት እንዳሉት በዘርፉ የሚታዩ የመጸዳጃ ቤት አያያዝ፣የመኝታ ክፍል ንጽህና፣የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት፣ባህል የማይገልጹ አለባበሶች፣በሙያው ያልተመረቁ ሰራተኞች በዘርፉ መሰማራታቸው ሰፊ ክፍተቶች እንደነበሩ አንስተዋል።

ስልጠናው በዘርፉ ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮች የሚቀርፍ ሲሆን ቀጣይ በስልጠናው መሰረት ወርደው እንደሚሰሩ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *