በዞኑ ወጣቶችና ህብረተሰቡ በማሳተፍ በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ አበረታች ተግባራት በክረምትም ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም በዘርፉ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳሰቡ።


የ2016 ዓ.ም የበጋ ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መዝጊያና የክረምት መክፈቻ መርሃ ግብር በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በመርሃ ግብሩ ተገኝተው እንዳሉት የጉራጌ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ በጌዝ፣ በደቦ፣ በእድር ቀድሞ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት ያለው ማህበረሰብ ነው።

ይህ የማህበረሰቡ የቆየ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶችን በመጠቀምና ወጣቶችን በማሳተፍ በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ አበረታች ተግባራት በክረምትም አጠናክሮ በመስራት አቅመ ደካማ ወገኖች በጊዜያዊነት ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ችግራቸውን በሚፈታ መልኩ ሁሉም በትኩረት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

በጎ ተግባር መስራት ከህሊና እርካታ ባለፈ በፈጣሪም ዘንድ ትልቅ ዋጋ ያለው በመሆኑ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በዞኑ አቅመ ደካማ ወገኖችን የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ተረጂ ወገኖችን እንዳይኖሩ በእቅድ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፈይሰል ሀሰን በበኩላቸው የማህበረሰቡ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶችን በመጠቀምና ወጣቶችን በማሳተፍ በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ስራዎች መሰራቱን ተናግረዋል።

በዞኑ በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ12 ዘርፎች 107 ሺህ 74 ወጣቶችን በማሳተፍ 307 ሺህ 2 መቶ 33 የማህበረሰብ ክፍሎችን ማስጠቀም ተችላል።

በዚህም ከመንግስት ይወጣ የነበረው ከ88 ሚሊዮን 7 መቶ ብር በላይ ማዳን መቻሉንም ገልጸዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ13 መስኮች 201 ሺህ 104 ወጣቶች በማሳተፍ 564 ሺህ 197 የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማስጠቀም መታቀዱንም ተናግረዋል።

ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን ባለሀብቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃድ ስራ በመሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አመላክተዋል።

የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብስራት ገብሩ እንዳሉት በወረዳው በበጋ በሁሉም መስኮች አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት ቤት በአዲስ የመገንባት፣ የማደስ ብሎም የደም ልገሳና ለወላጅ አጥ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።

በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 7ሺህ 575 ወጣቶችን በማሳተፍ 20ሺህ 2 መቶ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው በዚህም ከመንግስት ይወጣ የነበረው ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችላል ብለዋል።

ይህ በጎ ተግባር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበጋው በሁሉም መስኮች የተከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ይበልጥ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።

በተለይም አቅመ ደካማ ወገኖች በመለየት ወጣቶችና የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የተሰራው ስራዎችን በክረምትም ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በእለቱም በከተማው የአንዲት አቅም ደካማ እናት ቤት በአዲስ ለመገንባት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ያስጀመሩ ሲሆን በሀዋሪያት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልም የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *