የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በመስክ ምልከታው ወቅት እንዳሉት በዞኑ በግብርና በሁሉም ዘርፍ የአርሶ አደሩ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው።
በተለይም በመኸር እርሻ ልማት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎና ሌሎችም ሰብሎች ከኩታ ገጠም አልፎ ሜጋ ክላስተር በሆነ መንገድ ማልማት መቻሉን አንስተው በዞኑ ደጋማ አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራና በኖራ በማከም የተሰሩ ስራዎችን ሞዴል ስራ መሰራቱና ይህም በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በዞኑ የእንደጋኝ ወረዳ አርሶ አደሮች የባለሙያ ምክረ ሃሳብ በተገቢው በመቀበልና ቴክኖሎጂ በተሟላ ሁኔታ ተጠቅመው በመስራታቸው ማሳዎቹ በምርጥ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዞኑ በሌማት ትሩፋት በእንሰሳት ዘርፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ላጫ በወረዳውም አርሶ አደሩ በዶሮ፣ በበሬ ማሞከት እየሰሩት ያለው ስራ አበረታች ነው ብለዋል።
በሌማት ትሩፋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የምግብ ስርአትን ከማሻሻል ባሻገር ገቢ ማስገኛ አዋጭ ዘርፍ መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በዘርፉ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ወቅቱን ያጠበቀ ዝናብ መከሰቱን ተከትሎ በዞኑ የደረሱ ሰብሎችን ወደ ጎተራ ለማስገባት አርሶ አደሩ፣ ተማሪዎችና ሌሎችም የተለያዩ አደረጃጀቶች በመጠቀም ምርት እንዳይባክን መሰብሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል በበኩላቸው በወረዳው በመኸር እርሻ ልማት አርሶ አደሩ የባለሙያ ምክረ ሃሳብ በመቀበልና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስንዴን በኩታገጠም ያለሙት ማሳ አበረታች ነው ብለዋል።
በዞኑ የሌማት ትሩፋት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ወጣቶች፣ አርሶ አደሩ በዘርፉ እየሰሩት ያለው ስራ አበረታች በመሆኑ በቀጣይም ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል።
ሰላም በእጄ፣ ብልጽግና በደጄ በሚል የተጀመረው ስራ የበለጠ ሊያጠናክር በሚችል መልኩ በወረዳው በተቀናጀ ግብርና እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አውስተዋል።
ወቅቱ ያልጠበቀ ዝናብ መከሰቱ ተከትሎ የደረሱ ሰብሎች ወደ ጎተራ ለማስገባት አርሶ አደሩ የቤተሰብ ጉልበት በመጠቀም ተማሪዎችና ሌሎችም አደረጃጀቶችን በመጠቀም ምርት ወደ ጎተራ ለማስገባት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የዞኑ ምክትል አስተዳደሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በዞኑ በስንዴ፣ በጤፍ፣ በገብስ፣ በአተር በባቄላና ሽንብራ ከ103 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።
በወረዳው አርሶ አደሩ፣ ባለሙያና አመራሩ ተቀናጅቶ በሰራው ስራ አበረታች የስንዴ ማሳ ማየታቸውን አንስተዋል።
በዞኑ በመኸር ከለሙ ማሳዎች ጤፍ ከ15 ሺህ 7 መቶ በላይ፣ ገብስ ከ16 ሺህ በላይ፣ ስንዴ ከ11 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በኩታ ገጠም ማልማት መቻሉን አንስተዋል።
በዘንድሮ አመት 5ሺህ 9መቶ ሄክታር በላይ ታርሶ የማይታወቁ መሬቶችን በማረስ በሰብል መሸፈን ተችሏል ያሉት ኃላፊው በዚህም በዘርፉ ውጤታማ ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።
ሌላኛው በሌማት ትሩፋት በወተት፣ በስጋ፣ አሳ፣ በእንቁላል መንደር የተጀማመሩ ስራዎች የተሻለ መሆኑን ጠቅሰው የእንቁላልና የወተት አቅርቦትን በማሻሻል የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ገበያው ለማረጋጋት የተጀማመሩ ስራዎች ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በወረዳው በሰብልና በዶሮ ዘርፍ የተሰማራው አርሶ አደር አለማየሁ ኤራቦ እንዳሉት ከሰብል ስራ ጎን ለጎን በሌማት ትሩፋት በዶሮ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም 650 ዶሮ በማርባት በዘርፉ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
የዶሮ እርባታ ስራ አዋጭ ነው ያሉት ራሱ ባሻገር ሌሎችም ወጣቶች በዘርፉ ለመስራት በአካባቢው የመብራትና የውሃ ችግር መኖሩንም ጠቁመዋል።