በዞኑ አሁን ያለዉን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሁሉም አካል በቅንጅት መስራት እንደሚገባው የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ የፀጥታ ጉዳዮች፣ የህግ ማስከበርና የሰላም ግንባታ ሥራዎች የመጀመሪያዉ ግማሽ አመት የአፈፃፀም ሪፖርት የዞኑ የጸጥታ ምክር ቤት አባላት በተገኙበት ግምገማና ምክክር በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።

የዞኑ የጸጥታ ምክር ቤት የዞኑ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራርና የጸጥታ አመራሩ በጸጥታና በህዝብ ደህንነት ቁልፍ ጉዳዮች ዙሪያ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ዉሳኔ የሚሰጥ አካል ነዉ።

በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ክፍሌ ለማ እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት የጸጥታው ምክር ቤት የህብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ በተሰሩ ስራዎች አበረታች ዉጤት ማምጣት ተችሏል።

በዚህም በምስራቅ መስቃን፣ማረቆ እንዲሁም ቆሴ አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን የአመራሩና የጸጥታ አካላቱ እንዲሁም የህብረተሰቡና ወጣቱ ሚና የጎ እንደነበረም አመላክተዋል።

የዞኑ ሰላም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሁሉም አካላት ለሰላምና ጸጥታዉ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አብራርተዋል።

ህዝቡን በማሳተፍ እና በየአካባቢዉ ያሉ በጎ ተሞክሮችን በሁሉም አካባቢዎች በማስፋትና ሰላም በማረጋገጥ ረገድ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አቶ ክፍሌ አክለውም የአካባቢ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ አመራሩ ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በዘርፉ ዘላቂነት ያለዉ ለዉጥ ማምጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ተካ እንዳሉት በዞኑ የሰላም ግንባታና ህግ ማስከበር እንዲሁም የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ተገቢዉን ትኩረት በመስጠት በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ተችሏል።

አሁን ላይ በዞኑ የተገኘዉን አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ቀጣይነት ባለዉ መንገድ ዉጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።

ሰላምና ጸጥታ በማረጋገጥ ዘርፍ ያሉ ጉድለቶችን በመለየት እና በቀጣይ አጽእኖት ሰጥቶ በመስራት የሚፈለገዉ ዉጤት እንዲመጣ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።

ህግ በማስከበር ጉዳይ ላይ ያሉ ችግሮችን በተገቢዉ የመቅረፍ ጉዳይ የሚመለከታቸዉ ባለ ድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአካባቢ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ አመራሩ ከአጎራባች አካባቢዎች እና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በዘርፉ ዉጤታማ ስራ መሰራት እንደሚገባም አስረድተዋል።

የግጭት ነጋዴዎች በሆነ ባልሆነም አጀንዳ በመንዛት ወጣቱንና ሌላዉን የህብረተሰብ ክፍሎችን ባልተገባ መንገድ ወደ አመጽና ሁከት እንዳይመሩ ህግ የማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ የቆየና ይህም በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነም አብራርተዋል።

በመድረኩ የተገኙ አንዳንድ የጸጥታዉ ምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት በየአካባቢዉ ለሚፈጠሩና ችግሮች የዞኑ የጸጥታዉ ምክር ቤትና ክልሉ ሊያግዝ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በአበሽጌ ወረዳ ህብረተሰቡ ከኦነግ ሸኔ ጋር በተያያዘ የሚነዙ ዉዥንብሮች በማስቀረት እንዲሁም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝዉዉር በማስቆም አርሶአደሩ ወደ ልማት መመለስ እንዳለበትም አስረድተዋል።

በምስራቅ መስቃንና ማረቆ እንዲሁም ቆሴ አካባቢ የተፈጠሩ ችግሮች እንዲቀረፉ ማህበረሰቡን ወደ ቀድሞ አንድነቱን ለመመለስ የተሰራ ስራ የሚበረታታ እንደሆነና በቀጣይም የህዝቡን ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ በቁሳቁስና በበጀት መደገፍ እንዳለበትና የፖሊስ አባላቶች ሪፎሮም መደረግ እንዳለባቸዉም አስተያየት ሰጪዎች አስታዉቀዋል።

ሰላምና ጸጥታ በማረጋገጥ በኩል እየተሰሩ ያሉ መልካም ጅምሮች በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋልሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *