በዞኑ በ2016 በጀት ዓመት በኮዋሽ ፕሮግራም የተከናወኑ ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን የዋና አስተዳዳሪና የኮዋሽ ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይና የአስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የኮዋሽ ፕሮግራም ተጠቃሚ በሆኑ ሁለቱ ወረዳዎች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ከዞን ጀምሮ የኮዋሽ ስትሪንግ ኮሚቴ በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ተግባራት በአግባቡ እየተከታተለ የመምራት ኃላፊነቱ እንደሚወጣ የገለጹት አቶ ደሳለኝ የዞን የበጀት መዋጮ በወቅቱ በመልቀቅ ጥራት ያለው ስራ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡

የኮዋሽ ፕሮግራም ተግባራዊ በሚደረግበት አካባቢ የሚገኙ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በኮዋሽ ፕሮግራም የተገነቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃና የንጽህና መጠበቂያ ግንባታዎች አስፋላጊውን እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አቶ ደሳለኝ አስገንዝበዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ውሃ ማዕድንና ኤነርጂ መምሪያ ኃላፊና የኮዋሽ ስትሪንግ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አየለ ፈቀደ በበኩላቸው በኮዋሽ ፕሮግራም ጌታና አበሽጌ ወረዳዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ በማሻሻል ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ክፍሎች፣ ሽንት ቤቶችና በትምህርት ቤቶች የእጅ መታጠቢያ ግንባታዎች መከናወናቸውን የገለጹት አቶ አየለ እነዚህ ስራዎች የሚሰሩት የኢትዮጵያና የፊላንድ መንግስት ትብብር በተገኘ በጀት ነው፡፡

ለኮዋሽ ፕሮግራም የፊላንድ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ የሚወሰነው የኢትዮጵያ መንግስት በሚያደርገው የበጀት መዋጮ ላይ የተመሰረት በመሆኑ ከክልል ጀምሮ ለተዛማጅ በጀት ወይም ማቺንግ ፈንድ የሚመደበው ገንዘብ ተሰብስቦ በወቅቱ ስራ ላይ እንዲውል ለወረዳዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ፕሮግራም በየዓመቱ ከ5 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የጠቆሙት አቶ አየለ በየደረጃው የሚገኘው የስትሪንግ ኮሚቴ ከዕቅድ ጀምሮ ስራዎች በጥራት መከናወናቸውን በመከታተል ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በመንግስት መደበኛ በጀት የማይሽፈኑና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው በኮዋሽ የሚገነቡ ግንባታዎች በተስማሚ ጊዜ ለማከናወን እንዲቻል የማቺን ፈንድ በወቅቱ እንዲለቀቅ ጠይቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *