የጉራጌ ዞን የምክር ቤት አባላት ካነሷቸው ጥያቄ መካከል በዞኑ በሁሉም ዘርፍ ህብረተሰቡን በማስተባበር የተከናወኑ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የተሻለ ቢሆንም የመካናይዜሽንና የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትና በአቅርቦቱ ላይ ያለው ህገወጥነት መፍታት ይገባል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የተሻለ መሆኑን ያነሱት አባላቶቹ በዘርፉ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የዞኑ ህብረተሰብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው የወልቂጤ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ መሰራት እንዳለበት አንስተዋል።
በፌደራል፣ በክልልና በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ ያደሩ ካፒታል ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይገባል ሲሉም አመላክተዋል።
በመንገድና በትምህርት ልማት ዘርፍ ማህበረሰቡን በማስተባበር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች እንደሆነ ጠቅሰው የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ስራ በማጠናከር በቀጣይ የትምህርትና የስራ ቋንቋ ለማድረግ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በዞኑ የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስና ህብረተሰቡ የማጤመ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።
ባህርዛፍ አንስቶ በፍራፍሬና በቋሚ ሰብል ለመሸፈን የተጀመረው ስራ በቀጣይ አስፍቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የወልቂጤ ከተማ የወሰን ጣልቃ ገብነትና የቆሴ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን መንግስት ሊፈታ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ጠይቀዋል።
ከዚህም ባለፈ የመንገድ ተደራሽነት፣ የኔትወርክ ችግር፣ በጤና ተቋማት ላይ የሚስተዋለው የመድሀኒት አቅርቦት ችግር፣ ብድር አመላለስ ላይ እንዲሰራ አንስተዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የተከበሩ አቶ ላጫ ጋሩማ በምላሻቸው በግብርና ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ያልታረሱ መሬቶችን በማረስ በሰብል ለመሸፈን እየተሰራው ያለው ስራ በቀጣይም በማጠናከር እንደሚሰራ ያነሱት አቶ ላጫ በባህርዛ የተሸፈኑ መሬቶችን በማንሳት በቋሚ ሰብልና በአትክልትና ፍራፍሬ ለመሸፈን የተጀመረው ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በፌደራልና በክልል መንግስት የሚሰሩ ካፒታል ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቁ እንደሚሰራ ጠቁመው በተለይም የከሬብ መስኖ እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ይሰራል ብለዋል።
በዞኑ መሬት ወስደው ሳያለሙ አጥረው ባስቀመጡ ኢንቨስትመንቶች ላይ የክትትል ስራ በማጠናከር እርምጃ ከመውሰድ ባለፍ ለአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የከተሞች ውበትና ጽዳት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ጠቁመው በዞኑ ከሰላምና ጸጥታ አንጻር አሁን ላይ ያለው አንጻራዊ ሰላም በማጠናከር መስራት ይገባል።
የወልቂጤ ከተማ የወሰን ጣልቃ ገብነትና የቆሴ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለመፍታት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
በመንገድና በትምህርት ልማት ዘርፍ ህብረተሰቡን በማስተባበር የተከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ በጤና ከእናቶችና ህጻናት ሞትና የወባ ወረርሽኝ ችግር ለመቅረፍ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።
በመጨረሻም የዞኑ አስተዳደር ምክር ቤት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2017 በጀት አመት ጠቋሚ እቅድ ለምክር ቤት አባላት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኃላ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።