በዞኑ ምክርቤት የጸደቀው በክልል የመደራጀት ጥያቄ እና ሌሎችም የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ጠየቁ።

ህዝቡ በየደረጃው የሚያነሳቸው የአደረጃጀትና ሌሎችም የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ብልፅግና ፓርቲ በጉባኤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ደረጃ በደረጃ ህዝቡ በማወያየትና በማሳተፍ እንደሚፈቱም ተገልፀዋል።

መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል የህዝብ ውይይቶች ዛሬ በዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ ጨምሮ በቡታጀራና በሌሎችም በ14 ማእከላት ውይይት ተካሄደዋል።

በዞኑ በተካሄዱ የህዝብ ውይይቶች የጉራጌ ዞን በክልል የመደራጀት ጥያቄ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የሚነሳ ሳይሆን ለረዥም አመታት ሲጠየቅ የነበረና በአፋኙ የህወሓት ስርዓት ምላሽ ሳያገኝ መቆየቱን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

አሁን በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ እየመራ ያለውን የብልጽግና ፓርቲ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያኙ እንደሚሰራ እምነቱ እንዳላቸው ገልፀው በጉባኤው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የጉራጌ ዞን በክልል የመደራጀትና ሌሎችም የልዩ ወረዳ ጥያቄዎች ህገ-መንግስታዊ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።

ነዋሪዎቹ እንደገለፁት በዞኑ ባለፉት የለውጥ አመታት በርካታ የልማትና መልካም ስራዎች መሰራታቸውና በዚህም ተጠቃሚ መሆናቸው ገልፀው አሁንም በርካታ ያደሩ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸው አንሰተዋል በዋናነትም የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ አለመሆኑ፣የገጠር ተደራሽ መንገዶች ችግር መኖሩ፣የማዳበሪያ ዋጋ መናር፣ የወልቂጤ ከተማ ወሰን ያለመካለል፣ የመብራት ተደራሽነት፣የመብራት ዲስትሪክት አለመኖርና መብራት መቆራረጥ የብልፀግና ፓርቲ መንግስት በትኩረት ሊፈታልን ይገባል ብለዋል።

የህግ የበላይነትና የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ መሆናቸው በተለይም የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴና ጥፋት ከህዋሀት እኩል ትከለረት የሚፈለረግ መሆኑ፣ በዞኑ የኢንዱስትሪ ፓርክ ባለመኖሩ ስራ አጥነት ለመቀነስ ተፅኖ መፍጠሩ፣ የወልቂጤ ዩኒቭርስቲ የቡታጀራ ካምፓስ ቃል ተገብቶ ረዥም ጊዜ ህዝቡ ምላሽ አለማግኘቱ ጠቅሰው እነዚህ የቆዩና ያደሩ ችግሮች አሳሳቢ መሆናቸው ተናግረዋል።

በአለም አቀፍና እንደ ሀገር የተፈጠረው የኢኮኖሚ ግሽበት ባሻገር ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት መኖሩና የቁጥጥር መላላት፣የወጣቶች የስራ አጥነት መበራከት፣የመምህራን እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አለመኖሩ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ሆስፒታሎች ተደራሽ አለመሆንና የቡኢ ሆስፒታል ደረጃ አለመሻሻል በተጨባጭ በዞኑ በትምህርት ጥራትና በጤና ስራ ተፀኖ እየፈጠረ መሆኑ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

አክለውም ነዋሪዎቹ በየተቋማቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መኖራቸው፣የተለያዩ ዘርፎች ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች መኖራቸው፣በአንድ አንድ መዋቅሮች የአመራር ስምሪትና ምልመላ ችግር ያለበት መሆኑ ተናግረዋል።

በዞኑ ለረዥም ጊዜ ተጀምሮ የተጓተተው የአጣጥ -ጉንችሬ -ቆሴ -ሌራ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣በዞኑ በሙህርና አክሊል፣ በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ፣በእንደጋኝ ወረዳና በሌሎችም የሚነሱ የፌደራል መንገድ ሆነው ዛሬም ድረስ አስፋልት ያላገኙ መንገዶችና ሌሎችም ችግሮች መንግስት ተገንዝቦ ህዝቡን በማሳተፍ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል የዞኑ ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዞን፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደር ደረጃ መፈታት የሚገባቸውን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመፍታት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ጀማል ገለጻ ህረተሰቡ የሚያነሳቸውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት፣ የኑሮ ውድነት መቀነስ፣ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ፣ የመንግስ አገልግሎት አሰጣጥ ፍትሃዊ እንዱሆን ማድረግ እንዲሁም ከአመራር ምደባና ስምሪት ጥራትና ሌሎችም የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ ወሰን የማካለል ጥያቄ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ወንድማማችነት ሊያጎለብት በሚችል መልኩ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ይፈታል ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የጉራጌ በክልል የመደራጀት ጥያቄ እና ሌሎችም የልዩ ወረዳ ጥያቄዎች ማህበረሰቡ በጠየቀበት መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ የዞኑ አመራር እየሰራ ነው ያሉት አቶ መሀመድ ጀማል ምንም ውይይት ባልተካሄደበት በክላስተር ተደራጅቷል ተብሎ የሚወራው ውሸት በሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም በዞኑ ማህበረሰብ የተጠየቀው የአደረጃጀት ጥያቄ የአመራሩም ጥያቄ በመሆኑ የብልጽግና ፓርቲ በጉባኤው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንዲያገኝ እንደሚሰራ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

ዛሬ በዞኑ የተካሄደው ውይይት እንዲመሩ ከተመደቡ አመራሮች መካከል የአማራ ክልል ም/ር/መስተዳድር ዶ/ር ጌታቸው ጀንበር ፣ በሚኒስቴር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ክቡር አምባሳደር ሀሰን አብድርቋድር፣ ወ/ሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ የብልፅግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል፣አቶ ስንታየሁ ሀሰን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና አማካሪና የደቡብ ክልል የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ ይገኙበታል።

ሁሉም የህዝብ ውይይቱ የተካሄደበት ዓላማ አስመልክተው እንደገለጹት ባለፉት የለውጥ አመታት የተከናወኑ የልማት፣ የዴሞክራሲ ግንባታና ሌሎችም ስራዎች በመገምገም ጉድለትና ጥንካሬዎች በመለየት በብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ተከትሎ ህብረተሰቡ ሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያለመ ነው።

አክለውም አወያዮቹ ህብረተሰቡ ያነሳቸው የአደረጃጀት ጥያወቄዎች፣ የአጣጥ -ጉንችሬ -ቆሴ -ሌራ የአስፋልት መንገድ ግንባታ መጓተት፣ የወልቂጤ ከተማ የመብራት ዲስትሪክት፣ የቡታጀራ ካምፓስ፣የኮሌጅና ሌሎችም ያደሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመንግስት በማቅረብ ደረጃ በደረጃ በእቅድ ምላሽ እንዲያገኙ ህዝቡን ያሳተፈ ስራ ይሰራል ብለዋል።

በተለያዩ ማእከላት ህዝቡ ሲያወያዩ የነበሩ አመራሮች ችግሮቹ በየደረጃው ህዝቡ በማሳተፍ ተገቢ እቅድ በማቀድ በቅደም ተከተል ከወረዳ ጀምሮ ሁሉም በየደረጃው በጊዜ የለንም መንፈስ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በመድረኮቹም በተነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲሁም ብልፅግና ፓርቲ በጉባኤው ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ተገቢ ማብራሪያ በመስጠት መግባባት በምፍጠር የተጠናቀቀ ሲሆን ወይዘሮ አለም ፀሀይ ጳውሎስ የብልፅግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል፣አቶ ስንታየሁ ሀሰን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና አማካሪ አቶ ክፍሌ ለማ የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪና የቡታጀራ ከተማ አመራሮች በቡታጀራ ከተማ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች ጎብኝተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ፣ የፈረሰውን እንገንባ፣ለፈተና እንዘጋጅ!

በመረጃ ምንጭነት ምርጫችሁ ስላደረጋችሁን እናመሰግናለን

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *