በዘንድሮ የመኸር ወቅት የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።


መምሪያው የ2015/16 የምርት ዘመን ዞናዊ የመኸር እርሻ ልማት ንቅናቄ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ በንቅናቄው መድረክ የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ህገወጥነትን ከመቆጣጠር ባለፈ የግብርናው ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መውጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ያልታረሱ የወል መሬቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ወጣቶችን አደራጅቶ ማሰማራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከወል መሬት በተጨማሪ በመንግስትና በእምነት ተቋማት የሚገኙ መሬቶች በማልማት መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ለማሟላት ሁሉም ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለበት አቶ ክብሩ ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው በመኸር እርሻ ንቅናቄ መድረኩ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ዘንድሮ የመኸር ወቅት ስራዎች አቀናጅቶ በመምራት የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የግብአት አቅርቦት እጥረት እንደ ሀገር ያለ መሆኑን ያነሱት አቶ አበራ ችግሩንም ለመቀነስ መምሪያው እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከሰብል ልማት ጎን ለጎን የእንስሳት ዘርፍ ምርታማነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመኖ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

አርሶ አደሮች መሰረታዊ የምግብ ፍጆታቸው ከማሟላት ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የገቢ አቅማቸው እንዲያሳድጉ የተጀመረው የ30-40-30 የፍራፍሬ ፓኬጅ ውጤታማ ለማድረግ በዘንድሮ አመት እያንዳንዱ አርሶ አደር በማሳው 40 የፍራፍሬ ችግኝ መትከል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በመምሪያው የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ የውይይት ሰነዱ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት በዘንድሮ የመኸር እርሻ ወቅት በተለያዩ ሰብሎች 168ሺህ 699 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 10 ሚሊዮን 841ሺ 455 ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል።

በዘርፉ የታቀደውን እቅድ ውጤታማ እንዲሆን በተቀናጀ መልኩ ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አቶ አክሊሉ ጡቁመዋል።

በመምሪያው የእንሰሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ ሙደሲር የእንሰሳት ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ የእንሰሳት ዝሪያ በማሻሻል ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የመኖ እጥረትና ጥራት ላይ በተቀናጀ መልኩ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የመድሩኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የመኸር እርሻ ስራ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።

የግብአት አቅርቦት ችግር አርሶ አደሩ እያማረረ እንደሚገኝ ጠቁመው ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በየአመቱ በአረንጓዴ አሻራ እየተሰራ ያለው ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው መትከል ብቻ ሳይሆን የጽድቀት መጠናቸውን ከፍ እንዲል ትኩረት ሰጥቶ መሰራት አለበት ብለዋል።

የንቅናቄው መድረክ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የፍራፍሬ መንደር በመመስረት የተሻለ ስራ እየሰሩ ሲሆን ቀጣይ ተግባሩን አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በእንሰሳት ዘርፍ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የመኖ ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበትም አመላክተዋል።

አርሶ አደሩ እየተፈታተነ የሚገኘው የግብዓት አቅርቦት እጥረት በምርትና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል ሲል የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *