በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ለማረም በዛሬው እለት ከጉራጌ፣ከምስራቅ ጉራጌ፣ከኦሮሚያ ክልል ከምራብ ሸዋ ዞን፣ከኦሮሚያ ክልል የትራንስፖርት ማህበር ቦርድ አመራር ፣ ከገላን ክፍለ ከተማ፣ከሰበታ ከተማ እና ከወሊሶ ከተማ የትራንስፖርት ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች ጋር በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት የትራንስፖርት ዘርፉ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚተገበሩበት ይሁን እንጂ ውስብስብ ችግሮችን በዛው ልክ የሚስተናገዱበት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመሆኑም በተለይ ትርፍ መጫን፣ትርፍ ማስከፈል፣መንገድ ላይ ማውረድ፣ደንብ መተላለፍ ስርአቱን ተከትሎ አለመስራት እና ሌሎችም የሚስተዋሉበት ሲሆን ችግሮች ለማረም እና ህግን ለማስከበር ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድባቸው አካላቶች ጉዳዮን ወደ ብሄር በማዞር የግል ጥቅማቸው ለማስጠበቅ የሚሰሩ አካላቶች ትልቅ ፈተና ሆነዋል ብለዋል።

አቶ ሙራድ አክለውም ማህበረሰቡ እርስ በራሱ የተጋመደ በመሆኑ በቀጣይም ለእነዚህ አካላቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ለመቅረፍ በተለይ የጉራጌ፣የምስራቅ ጉራጌ እና የምራብ ሸዋ ዞንና በዘርፉ የሚሰሩ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ከአጎራባች ዞኖች ጋር በትኩረት እንደሚሰራ የገለፁት አቶ ሙራድ ችግሮች ካሉ አስቀድሞ ማጥናት ፣መረጃ መለዋወጥና የእርስ በርስ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር፣መግባባትና መወያየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ በበኩላቸው የትራንስፖርት ዘርፍ ችግር ለመቅረፍ አሰራርን ተከትሎ መሄድና ህግን ማስከበር ወሳኝ ተግባር ነው።

በትራንስፖርት ዘርፍ ብዙ ውስብስብ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን ወንድማማችነትና እህተማማችነታችን ማጠናከር ፣ችግር ፈቺ የሆኑ ሀሳቦችን በማቅረብ ህብረተሰቡ የሚፈልገው አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

አቶ አለማየሁ አክለውም ህግን ሲከበር በምክንያት እና በአሰራሩ መሰረት መሆን አለበት ያሉ ሲሆን በዞኑ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች በአፋጣኝ ለመቅረፍ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የምራብ ሸዋ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ሺፈራው እንደገለፁት የጉራጌ እና የኦሮሞ ማህበረሰብ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮቻቸው በጋራ የሚያከናዉኑ እንደመሆናቸው መጠን ለዚህም የትራንስፖርት ዘርፉ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የማህበረሰቡ የእርስ በርስ ግንኙነት እጅግ የጠነከረ እና ቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አቶ አለማየሁ አስገንዝበዋል።

ይሁን እንጂ በትራንስፖርት ዘርፉ ህብረተሰቡ ለባሰ እንግልት የሚያደርሱና ለራሳቸው ጥቅም የሚሰሩ ህገ ወጦች መርህ ለማሰያዝ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

አቶ አለማየሁ አክለውም ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በተለይ ሹፌሮች፣እረዳቶች፣የስምሪት እና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች ጥሩ ስነ_ምግባር የተላበሱ መሆን እንዳለበቸው አስታውቀዋል።

በሶስቱ መዋቅሮች አሽከርካሪዎች የሚያነሱት የፍትሀዊነት ችግር ለመቅረፍ የሶቱም መዋቅር አመራሮች እና የዘርፉ ባለሙያዎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሺፈራው ቀሪ ችግሮች ለማወቅ ጥናት ማድረግ፣መረጃ በአፋጣኝ መለዋወጥ፣በመናኸሪያ ውስጥ የሚሰሩ ህገ ወጦችን ማጽዳት፣ውይይቶችን ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በውይይቱ የተሳተፉ አካላት እንደገለፁት ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማዘመን እና ህገ ወጦችን ለይቶ ህጋዊ መሰረት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

አሽከርካሪዎች የሚያነሱት የፍትሀዊነት ችግር በትክልም ካለ መረጃ መሰብሰብ፣ጥናት ማድረግ ፣ህገ ወጦችን በጋራ መታገል፣ አጀንዳቸው ማክሰም እንደሚያስፈልግ በሰፊው አንስተዋል።

በመናኸሪያ ውስጥ አገልግሎት በፍትሀዊነት፣በእኩልነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሆን አለበት ያሉት ሀሳብ ሰጪዎቹ ለዚህም የመኪና ማህበራቶች ኃላፊነታቸው መወጣት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ሶስቱም መዋቅሮች የሚያገናኙ መስመሮች የጋራ መስመሮች ቢሆኑም የግላቸው ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ የሚሰሩ በመኖራቸው በጋራ መታገልና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

በእለቱም የወልቂጤ ከተማ መናኸርያ አገልግሎት አሰጣጡን የተጎበኘ ሲሆን ከዚህ በፊት የነበረው ችግር ተቀርፎ አሁን እየመጣ ያለው ለውጥ እጅግ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *