“በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለፍትሕ ያደረጉት የ‘#በቃ’ ዘመቻ ታሪካዊ ጀግንነት ነው”፦ አቶ ደመቀ መኮንን


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለፍትሕ ያደረጉት የ‘#በቃ’ /‘#NoMore’/ ዘመቻ ታሪካዊ ጀግንነት መሆኑን ተናገሩ።

አቶ ደመቀ የሀገርን ጥሪ ተቀብለው ከመላው ዓለም ወደ ሀገር ቤት የመጡ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እንኳን በሰላም መጣችሁ በማለት በወዳጅነት አደባባይ በተዘጋጀው መርሐ-ግብር ላይ ምስጋና አቅርበዋል።

“በየዘመኑ በውድ ልጆቿ ትብብር እና አይበገሬነት የተደቀነባትን ፈተና ሁሉ እየተሻገረች እዚህ የደረሰችው እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም ማህፀነ ለምለም የጀግኖች መፍለቂያ መሆኗን በተግባር አረጋግጣችኋልና ሀገር እና ወገን በእናንተ መኩራቱን ስገልጽ በኩራት ነው” ብለዋቸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለሀገሩ የተለያዩ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በዓለም አደባባይ ቅሬታውን ሲገልጽ እና ሲቃወም አጥብቆም ሲዋጋ መቆየቱንም አውስተዋል።

በተለይም በአሁኑ ሰዓት በቃ ወይም /#NoMore”/ በማለት ከጀግኖች አባቶቻችን በወረስነው ጀግንነት የጀመራችሁት የፍትሐዊነት ትግል ይሄን አድሏዊ ዓለም እርቃኑን አስቀርቷል ብለዋል።

የዳያስፖራው ትግል ለፓንአፍሪካኒዝም ወኔ መሆኑን እና አፍሪካን እና የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆችን ማነቃነቁን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

በሀገር ቤት ያለው ሕዝብ ለሀገሩ ዘብ በመቆም ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ሁሉን አቀፍ ርብርብ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አብራርተው፣ ይሁንና አሸባሪው ህወሓት የእኛን ልዩነት ከሚፈልጉ የጥፋት ኃይሎች እና ጠላቶቻችን ጋር አብሮ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሆን ሀገራችን ላይ ያልፈጸመው ጥፋት የለም ነው ያሉት።

አሸባሪው ቡድን በርካታ አሳዛኝ እና ዘግናኝ ድርጊቶችን መፈጸሙን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልል ልዩ ኃይሎች አሸባሪውን ኃይል በመደምሰስ ረገድ ዘመን ተሻጋሪ ጀግንነት ፈጽመዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ደማቅ መሥዋዕትነት በመክፈል ሀገራቸውን መታደግ ችለዋልና ልንኮራ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የደረሰብንን ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት ለመቋቋም እና ለማደስ ድጋፍ ለሚሻው ወገን እና መልሶ መገንባት ሥራ በተባበረ ክንዳችን አብረን መቆም ይገባናልም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

መረጃዉ ከebc ተገኘ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *