በወጣቶች የተጀመሩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል ህብረተሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታ ሁሴን ገለፁ።

በወረዳው መሃል አምባ ከተማ ነዋሪ አቅመ ደካማ አረጋዊያን ለሆኑት አቶ ሸምሱ ከማል ባለ 56 ቆርቆሮ አዲስ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ – ግብር በዛሬው እለት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታ ሁሴን ተገኝተው አስጀምረውታል።

በዚህ ወቅትም የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታ ሁሴን ባደረጉት ንግግር እኛ ኢትዮጽያውያን በአለም ህዝቦች ፊት በቀዳሚነት ከምንታወቅባቸው አኩሪ እሴቶች መካከል እርስ በርስ ያለን መተሳሰብ ፣ መረዳዳት እና መደጋገፍ አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።

በ2014 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ 16 የተመረጡ መስኮች ከ40 ሺህ 360 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማስጠቀም መጠነ – ሰፊ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ሲሆን ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን አዲስ መኖሪያ ቤት ግንባታ እና እድሳት በዋናነት እንደሚገኝበት ገልፀዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ጠንካራ መደጋገፍ እና መልካም እሴቶችን በሁሉም ዘርፎች ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከባለፉት ጊዜያት በተሻለ መልኩ በዘንድሮ አመት ከፍተኛ መነቃቃት ስለመፈጠሩ ያወሱት አቶ ሚፍታ ሁሴን ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በዛሬው እለት የተጀመረው የአቶ ሸምሱ ከማል አዲስ መኖሪያ ቤት ግንባታም ሆነ በየቀበሌው የሚከናወኑት ተጠናቀው ለአገልግሎት እስከሚበቁበት ጊዜ ድረስ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።

ወጣት ሚፍታ ረሻድ እና ጅላሉ ደንበል በበጎ ተግባሩ ላይ ሲሳተፉ ካገኘናቸው ወጣቶች መካከል ይገኙበታል እኛ ወጣቶች ያለንን እምቅ እውቀት፣ጉልበትና ጊዜያችንን ለበጎ ተግባራት በማዋልም ሆነ በዘርፉ የተያዙ ግቦችን ማሳካት እንዲቻል የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ከሌሎቹ የበጎ ስራዎች በተጨማሪ በዛሬው እለት የተጀመረውን የአቶ ሸምሱ ከማል መኖሪያ ቤት ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁለንተናዊ ተሳትፏችንን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም ተናግረዋል።

የመሀል አምባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሸምሱ ከማል በአነስተኛ ገቢ ማስገኛ ስራ ተሰማርተው ልጆቻቸውን እያሳድጉ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም በነበረባቸው የመኖሪያ ቤት ችግር ምክንያት በፀሃይ እና በዝናብ መፈራረቅ የተነሳ ቤተሰባቸው ለተለያየ ህመምና ለእንግልት ሲዳረጉ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ የወረዳው መንግስት፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እና ወጣቶች ችግራቸውን ለመፍታት እያደረጉት ባለው ድጋፍና ትብብር የተሰማቸውን ደስታና ምስጋና በዱአ ገልፀዋል ሲል የዘገበው የወረዳው የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን :-
Facebook:-https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *