በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና በዞኑ ትምህርት መምሪያ ትብብር በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ተማሪዎችና ወላጆች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለጸ።


የማጠናከሪያ ትምህርቱ በጉራጌ ዞን በተመረጡ በ12 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ሲሆን ከ4ሺ 160 በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በጉራጌ ዞን በተለያዩ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት የሚማሩ ተማሪዎች በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት ተማሪዎች የተፈጠረላቸው መልካም እድሎች በመጠቀም የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ልምዳቸው አካፍለዋል።

በመሆኑም ሁሉም ነገር በትምህርት እንደሚሆን፣ ስለ ትምህርት ያላቸው አመለካከት እንዲያስተካክሉ፣ ከልፋት በኋላ ውጤት እንዳለና ተማሪዎችም ነገን ተስፋ አድርገው እንዲማሩ መክረዋል።

ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸው ለትምህርት እንዲያውሉ እና ወላጆችም ልጆቻቸው በመቆጣጠር ለተማሪዎች ስነ ምግባርና ውጤት ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል ።

ዩኒቨርስቲው ለጉራጌ፣ ለምስራቅ ጉራጌ፣ ለየም ዞኖችና ለቀቤና ልዩ ወረዳ በተመረጡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቲቶሪያል እንደሚሰጥ የገለጹት ዶክተር ፋሪስ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ያለው የሰው ሀይልና እውቀት ተጠቅሞ ለትምህርት ጥራት የሚያደርገው ተሳትፎ በሁሉም አካባቢዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

አክለውም የትምህርት ውጤት እንዲሻሻል የትምህርት መሰረተ ልማት መሟላት እንዳለበትና በአሁን ወቅት ለዘርፉ ህብረተሰቡና መንግስት እያደረጉት ያለው ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት አሳስበው ዩኒቨርስቲውም የበኩሉ እንደሚወጣ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያና የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የስራ ሀላፊዎች በጋራ በመሆን እየሰጡት ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት በእኖር ኤነር መገር ወረዳ የመገር ዌራ እና በእኖር ወረዳ በተርሆኘ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የመማር ማስተማሩን ምልከታ አድርገዋል

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማረያም በዚህ ወቅት እንዳሉት ቲቶሪያል ትምህርቱ ከመሰጠቱ በፊት ለመምህራኖች ስልጠና እና ሌሎች አስፈላጊ የሆነ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ አስታውሰዋል።

በዞኑ 69 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን 63 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ይሰጣሉ ያሉት አቶ መብራቴ የቲቶሪያል ትምህርቱ ደግሞ በተመረጡ በ12 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ከ4ሺ 160 በላይ ተማሪዎች እየወሰዱ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ቲቶሪያሉ መምህራኖች ያላቸው እውቀትና ልምድ ለተማሪዎች የሚሰጡበት በመሆኑና የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር እንዲሻሻል ከፍተኛ ሚና አለው ነው ያሉት።በመሆኑም ተማሪዎችና ወላጆች እንዲሁም የትምህርት አመራር ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አስገንዝበው ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ኃላፊው አክለውም የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በዞኑ ለትምህርት መሻሻል እያደረገ ያለው ጥረት ከፍተኛ ሲሆን በተለይ የትምህርት ቁሳቁስ፣ የስልጠና፣ የመጽሀፍ ህትመት፣የቲቶሪያል እና የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግ በርካታ ድጋፎች እያደረገ በመሆኑ ኃላፊው ምስጋናቸው አቀርበዋል።

መምህር ሙሉጌታ ገዛኸኝኛ የአበሩስ ወልቂጤ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሲሆኑ ጌታሁን ብርሀኑ ደግሞ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው። መምህራኑ በጋራ እንደተናገሩት የቲቶርያል ትምህርቱ መምህራን እውቀታቸውንና ልምዳቸው ጭምር ለተማሪዎች የሚያስጨብጡበት መሆኑና ተማሪዎች ደግሞ በቀጣይ የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ እንዲሁም የበለጠ እውቀት እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

ተማሪ መዲና ኑረዲን፣ተማሪ ኢብራሂም ዘኪርና ምንተስኖት ፍቃዱ የቲቶሪያል ትምህርት ሲወስዱ ያገኘናቸው ናቸው።በጋራ በሰጡት ሀሳብ ወልቂጤ የኒቨርሲቲና የዞኑ ትምህርት መምሪያ ይህን እድል ማመቻቸቱ ለውጤታችን መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ይህን እድል ያገኙ ተማሪዎች ሳይዘናጉ ጊዜያቸው ለትምህርት በመስጠት የቲቶሪያል ትምህርቱ በአግባቡ ሊማሩ እንደሚገባ ያሳሰቡት ተማሪዎቹ መሰል አይነት እድሎችን ተጠቅመው በመስራት ለተሻለ ውጤት በርትተን እንሰራለን ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *