በወልቂጤ ከተማ የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊና ትውፊቱ በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከበረ።

ህዝበ ክርስቲያኑ ከሚያለያዩ ክፉ ስራዎች በመራቅና ወደ ጽድቅ በሚወስዱን ተግባራት ላይ በማትኮር ለሀገር ሰላምና አንድነት መስራት እንደሚገባ የጉራጌ፣የምስራቅ ጉራጌና የማረቆ ልዩ ወረዳ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ መልከ ጼዲቅ ተናገሩ።

የጉራጌ፣የምስራቅ ጉራጌና የማረቆ ልዩ ወረዳ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ መልከ ጼዲቅ እንደተናገሩት በጥምቀት በዓል መላው የሰው ልጅ በሙሉ የእዳ ደብዳቤው ተቀዶለት ነጻ የወጣበትና ሚስጢር የተገለጸበት እለት በመሆኑ ምእመናኑም ተንኮል፣ቂም በቀል፣ዘረኝነት ጸብንና ክፉ ስራዎችን በመተው ለጽድቅ ስራ መትጋት እንዳለባቸው መክረዋል።

አክለውም በዓሉ ሀይማኖታዊም ባህላዊም ሲሆን መንፈሳዊ አግልግሎት የሚከናወንበትና የማህበረሰቡ አብሮነትና መቻቻል የሚገለጽበት ታላቅ በዓል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ብሎም ለአለም እድገትና ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች ያሉት ብጹእ አቡነ መልከ ጼዲቅ ለአብነትም የመስቀልና የጥምቀት በዓል በዩኒስኮ መመዝገብ መቻላቸው አንዱ የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በባዓሉ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት የጥምቀት በዓል በሀገራችን ብሎም በዞናችን በድምቀት የሚከበር ታላቅ የአደባባይ በዓል ነው ብለዋል።

ዛሬ ላይ በዞናችን በሁሉም አካባቢ በቤተ-ዕምነቶች መካከል እየተስተዋሉ ያሉ የመቻቻል፤ የአብሮነትና የመተባበር በጎ ምግባሮቻችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ብለዋል፡፡

በጉራጌ ዞን እየተለመደ የመጣው የክርስቲያን በዓል ሲከበር ህዝበ ሙስሊሙ ለበዓሉ ድምቀት ከፍተኛ አስዋፅኦ የሚያደርግበት እንዲሁም የሙስሊም በዓል ሲከበር የክርስትና እምነት ተከታዮች ለበዓሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱበት በመሆኑ ይህን መልካም እሴት ይበልጥ ሊጠናከርና ለሌላው አካባቢ አርዓያ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው በበኩላቸው በዓሉ ስናከብር እርስ በርሳችን ተዋደን፣ተከባብረን እና ተረዳድተን መሆን አለበት ያሉ ሲሆን በጋራ ሰርተን የወልቂጤ ከተማ ሰላሟ የተረጋገጠና የበለጠ እንድታድግ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት ሀሳብ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ስርአቱ በተጨማሪ የህብረተሰቡ የመቻቻል የአብሮነት እሴት የሚንጸባረቅበት በዓል ነው ብለዋል።

አያይዘውም ከበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ከሌሎች የእምነት ወንድሞች ጋር በጋራ በመሆን የጽዳትና ሌሎች ስራዎችም ሲሰሩ እንደነበር የገለጹ ሲሆን መሰል አይነት በጎ ተግባራቶችን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምረያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *