በወልቂጤ ከተማ የሚገነባዉ የአረጋዉያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል የሁሉም የህብረተሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገዉ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ በጉብሬ ክፍለ ከተማ የአረጋዉያን ማዕከል ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ በዛሬዉ እለት የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ተቀመጠ።

በመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንዳሉት መቄዶንያ በሀገር ደረጃ እየሰራዉ ያለዉን ስራ የሚመሰገንና አርአያነት ያለው ብሎም የመንግስትን ክፍተት በመሙላት በማህበረሰቡ ላይ ያሉ ችግሮችን እየፈታ ይገኛል።

የመቄዶንያ የአእምሮና አረጋዉያን ማገገሚያ ማዕከል በዞናችን በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑ አረጋዉያንና የአእምሮ ህሙማንን በመቀበል ባለፉት አመታት ሰፊ ስራዎች እየሰራ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

በዞኑ ወልቂጤ ከተማ በጉብሬ ክፍለ ከተማ የሚገነባዉ የአረጋዉያን ማዕከል ለክልሉና ከዞኑ አልፎ ለሌሎቹም ዞኖች የሚጠቅም እንደሆነም ገልፀዋል።

ማህበረሰብ አቀፍ የሆኑ ትልልቅ ተቋማት የህብረተሰቡን ችግር በስፋት የሚቀርፉ በመሆናቸው ይህ ተቋም ወደ አካባቢያችን መምጣቱ የአካባቢዉ ማህበረሰብ በደስታ የተቀበለው ሲሆን ለዚሁ ለተቀደሰዉ ግንባታ የሚዉል መሬት ያመቻቸዉ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደርና ለሌሎችም ድጋፍ ላደረጉ አካላት አመስግነዋል።

ለግንባታዉ ስኬታማነት የዞኑ መንግስትና ህዝብ በማስተባበር ተቋሙ እዉን እንዲሆን ሰፊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ተወካይ አቶ ማርክነህ ዋልቶሬ እንዳሉት የመቄዶንያ የአረጋዉያንና የአእምሮ ህሙማን ማህበር በሀገር ብዙ ታአምር የሚመስሉ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ላይ ዛሬ የተጣለዉ የአረጋዉያ ማዕከል ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ የአረጋዉያንን ችግር በዘላቂነት የሚፈታ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

አረጋዉያን ለሀገራችን ብዙ ታሪክ የሰሩና ሀገራችን ዛሬ ለደረሰችበት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ እንደሆኑም ተናግረዉ እነዚህ አረጋዉያን መንግስት ዝም ብሎ ሜዳ ላይ እንዳይወድቁ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነም አስረድተዉ መቅዶንያ የአረጋዉያንና የአእምሮ መረዳጃ መዕከል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ቢኒያም በለጠ የአባቱን መሬት አሳልፎ ለዚህ በጎና የተቀደሰ አላማ በማዋል አርአያ በመሆኑ ከፍተኛ ምስጋናም አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሸሚማት ለሻድ እንዳሉት ግንባታዉ በ2 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ የአረጋዉያን ማዕከል ሲሆን ከ5 መቶ በላይ ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ አረጋውያንና የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚይዝም አብራርተዋል።

ለአረጋዊያኖቻችን ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ ተቋም መሰረት በመጣሉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸዉም አብራርተዉ የማእከሉ መስራች ዶክረተር ቢንያም በለጠን አመስግነዋል።

ለግንባታዉ ስኬታማነት የመንግስት ፣ የባለሀብቱ ፣ የመላዉ ህብረተሰብ ርብርብ እንደሚያስፈልገዉም አስረድተዋል።

በመቄዶንያ የአረጋዉያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል የአረጋዉያን ኮሚቴ ሰብሰቢ ሻምበል ደቦጭ ተስፋዬ እንዳሉት ማዕከሉ በመንግስት ይሁን በራሱ ምንም አይነት ፈንድ የለዉም ብለዉ ተቋሙ መጥተዉ በሚጎበኙት የህብረተሰብ ክፍሎችና እጃቸዉን በሚዘረጉ ወገኖች በሚያደርጉት ድጋፍ ነዉ የሚተዳደረዉ ብለዋል።

መቄዶንያ ማዕከል ተስፋ የቆረጡትን ወገኖችን ከመንገድ አንስቶ ተስፋቸው እንዲለመልም እያደረገ ይገኛል ብለዉ አዲስ አበባ ላይ በማዕከሉ ወደ 6500 ወገኖች እንደሚገኙና በ2013 አመተ ምህረት ብቻ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በ9 የአረጋዉያንና የአእምሮ ማዕከል መክፈታቸዉም አስረድተዋል።

ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ 8161 ok ብለዉ በመላክ የቻሉትን ድጋፍ በማድረግ ወገኖቻችን እድንታደጋቸዉ ብለዋል።

በመሰረተ ድንጋይ ማኖር ስነስርአቱ ላይ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል፣የመቄዶንያ የአረጋዉያንና አእምሮ መረጃ ማዕከል ተወካይ፣የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል፣የደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ተወካይ አቶ ማርክነህ ዋልቶሬ እንዲሁም የዞኑ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዬች መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ሸሚማት ለሻድና ሌሎችም ተገኝተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነዉ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *