በወልቂጤ ከተማ የሚነሱ የልማት፣የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የከተማው ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊያግዙ እንደሚገባ የከተማው አስተዳደር አሳሰበ።

ሰኔ 17/2015

በወልቂጤ ከተማ የሚነሱ የልማት፣የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የከተማው ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊያግዙ እንደሚገባ የከተማው አስተዳደር አሳሰበ።

የከተማው ልማትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከመንግስት ጎን በመሆን በጋራ እንደሚሰሩ የወልቂጤ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

በዛሬው እለት በሰላም በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙርያ ከወጣቶቹ ጋር በወልቂጤ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ወልቂጤ ከተማ ከተቆረቆረች 125 አመት አስቆጥራለች።በስም የዞኑ መቀመጫ ትሁን እንጂ በመሰረተ ልማት ስራዎች አዳዲስ ነገሮች ማየት ብርቅ እየሆ መጥቷል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት ወጣቶች እንደተናገሩት ከተማዋ ተለውጣ፣ሰላምዋን ተረጋግጦ፣ ውብና ማራኪ ለኑሮ አመቺ ሆና ለማየት ሁሉም ሰው የእለት እለት ምኞቱ ይሁን እንጂ ይህንን መየት ግን አልቻለም ይላሉ።

ለአብነትም በከተማው ለወጣቱ የስራ እድል ባለመፈጠሩ ወጣቱ ለሱስ እንዲጋለጥ እንዲሁም ከአካባቢው እንዲሰደድ ምክንያት እየሆነ ነው።

ከተማው ከዚህ በፊት ይታወቅበት የነበረው የሰላም ስም አሁን ላይ የደበዘዘ በመሆኑ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ህግ የማስከበር ስራ በመላላቱ የተነሳ የሚፈለገው ውጤት ማየት ስላልተቻለ የጸጥታ ተቋማት ከመቼውም በላይ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርና የወልቂጤ ከተማ ድንበር ወሰን እንዲካለል ሁል ጊዜ ለሚመለከተው አካል ቢነገርም እስካሁንም ችግሩ አልተቀረፈም ያሉት ወጣቶቹ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።

የከተማው አመራር እንዲሁም ወጣቱ አንድ ሆኖ እንዳይሰራ በሀይማኖት፣በዘር፣በመንደር፣በጎሳ በህገ ወጥ አደረጃጀት በማሰማራትና እርስ በርስ በመከፋፈል አንድ እንዳይሆንና ከተማዋ እንዳታድግ ተደርጓል።

ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ግጭትን የሚያባብሱ፣የከተማዋ ሰላም እንዳይረጋገጥ የሚያደርኩ አካላት ተበራክቷል ያሉት ወጣቶቹ በማናኛውም ዘርፎች ህግ በሚጥሱ አካላት ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ አስታውቀዋል።

ልማቶች እንዲፋጠኑ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከግል ተቋማት፣ከተራዶ ድርጅቶችና ከባለሀብቶች ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ ወጣቶቹ ጠይቀዋል።

የወልቂጤ ሆስፒታል ስራ አልመጀመሩ፣በጤና ተቋማት የመድሀኒት እጥረት መኖሩ፣የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በወቅቱ አለማጠናቀቅና የገቢ ስወራ መኖራቸው የከተማው ህብረተሰብ አስቆጥቷል ብለዋል።

የጉራጌ የአደረጃጀት ጥያቄ በህግ አግባብ የሚመለስ እንጂ በሁከትና በብጥብጥ የሚመለስ ባለመሆኑ ይህንን ተገን አድርገው ልማት የሚያደናቅፉ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ የተናገሩት ወጣቶቹ የከተማው ልማትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከመንግስት ጎን በመሆን በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው በምላሻቸው ለማንኛውም ነገር መሰረቱ ሰላም በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ሊሰራ ይገባል።

መንግስትም ሰላምና ጸጥታ ለማሰከበር፣የከተማው የማልማትና እኩል ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል።

ወልቂጤ ከተማ ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግና ጥሩ ስራ ሰርቶ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም በእኔነት ስሜት ሊያለማትና ሊጠብቃት እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን አደረጃጀት ምክንያት አድርገው ከተማዋን እንዳትለማና ሰላም እንዳትሆን የሚያደርጉና የሚያናፍሱ ህገ ወጥ ተግባራት የሚያከናውኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል ።

ከወጣቶቹ ለተነሱ ሀሳቦች ትክክል መሆናቸው የገለጹት አቶ እንዳለ በከተማዋ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ለማስጨረስ ከዚህ በፊት የነበሩ ውዝፍ እዳዎች መኖራቸውና የከተማው ወጪና ገቢ ባለመጣጣሙ ትልቅ ፈተና ሆኖዋል ብለዋል።

አክለውም ከተማዋ የበለጠ እንዳትለማ አንድ አንድ የኢንቨስትመን ቦታዎች በህገ ወጥ አካላት ተይዘው እንደነበረና ሊለሙ እንዳልተቻለ አመላክተው መሰል አይነት ህገ ወጥ ድርጊቶች ሲከናወኑ ወጣቱና ማንኛውም ህብረተሰብ ሊታገል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቅርብ ጊዜ በከተማው በተደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች አበረታች እንቅስቃሴዎች ታይቷል ያሉት ከንቲባው ለአብነትም የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የቁፋሮና የመስመር ጥገና እንዲሁም የጽዳት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ አንስተዋል።

የከተማው የድንበር ወሰን ማካለል ስራ በአርሶ አደሮች ላይ የተሰራው ክፉ አመለካከት በማስተካከል ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። ከተማዋ የበርካታ ብሔርና ብሔረሰቦች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት በመሆኑ ከተማዋ እንድታድግ ሁሉም የእኔነት ስሜት በመላበስና መተጋገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

አቶ እንዳለ አክለውም በከተማዋ የሚነሱ የልማት፣የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ወጣቶቹ የበኩላቸው ሊወጡ እንደሚገባ መክረው የከተማው አመራርም ህዝቡ ለጣለበት ኃላፊነት ለመወጣት በትኩረት የሰራል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ሙባረክ አህመድ በንግግራቸው ከዚህ በፊት በተሰሩ ስህተቶች የመንግስትና የህዝብ ግንኙነት ላልቷል።

ይህን ችግር ለማረምረና የከተማዋ ሰላምና ልማት ለማምጣት ባህላዊ እሴቶቻችን ጠብቀን በመከባበር፣አንድ በመሆን ፣በመደማመጥና በመቻቻል በጋራ ልንሰራ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ሶሻል ሚዲያው ለክፉ ነገር ከምንጠቀምበት ይልቅ ለመልካም ነገር በማዋል ወጣቱና መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክረው መስራት እንደሚገባ አቶ ሙባረክ አህመድ አሳስበዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *