በወልቂጤ ከተማ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረዉ ስራኖ ዘመናዊ ባለ አምስት ወለል ሆቴል ግንባታ በቀጣይ ለሌሎች ባለሀብቶች ተነሳሽነት የሚፈጥር እንደሆነም የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል አስታወቁ።

መስከረም 16/ 2015 ዓ.ም

በወልቂጤ ከተማ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረዉ ስራኖ ዘመናዊ ባለ አምስት ወለል ሆቴል ግንባታ በቀጣይ ለሌሎች ባለሀብቶች ተነሳሽነት የሚፈጥር እንደሆነም የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል አስታወቁ።

በ180 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባዉ ባለ አምስት ፎቅ ግንባታ በዛሬዉ ዕለት የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ፣የሀይማኖት አባቶች ፣የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ስራውን በይፋ አስጀምረዋል።

በእለቱ ሪቫን ቆርጠዉ ስራ ያስጀመሩት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንዳሉት የዞኑ ማህበረሰብ በተለያዩ አካባቢዎች የልማት ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።

በአካባቢያቸዉ ልማትና ሰላም ላይ ብዙ ዋጋ የሚከፍሉ ተወላጅ ባለሀብቶች በዞኑ በርካቶች ናቸዉ ብለዉ ከነዚህም ባለሀብቶች መካከል የወጣት ባለሀብት ዩሀንስ ሀይሌና ቤተሰቦች አንዱ እንደሆኑም አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ብዙ አምባሳደር አለዉ ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በተሰማሩበት ዘርፍ ባሉበት አካባቢ ላይ የህዝባቸዉ አምባሳደር በመሆን የተሰጣቸዉን የኢንቨስትመንት ቦታ በማልማት ፣ የተሰጣቸዉን የከተማ መሬት በማልማት በሌሎች አካባቢዎች ላይ ኢንቨስትመንት በማሳረፍ ህዝቡ ታታሪና ሰራተኛ እንደሆነም በተሰጣቸዉ ቦታ ላይ ብዙዎች ዉጤታማ ሆነዉ አካባቢ እየቀየሩና እያለሙ ያለበት ሁኔታ ህዝባችን በሁሉም ቦታ ክብር እንዲሰጠዉ አድርጓል ብለዋል።

በዞኑ መንግስት ያልደረሰባቸዉ ሰፋፊ የልማት ክፍተቶችን ለመሸፈን በአመት ዉስጥ ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ተወላጅ ባለሀብቱ በመንገድ መሰረተ ልማት፣በዉሃ በትምህርት ቤትና በጤና ተቋም ግንባታ ኢንቨስት በማድረግ የልማት ስራዎች እያከናወኑ እንደሆነም አብራርተዋል።

ተወላጅ ባለሀብቶች ህብረተሰቡን በሚጠቅሙ ስራዎች ላይ ሰፊ ጥረት በማድረግ እየሰሩበት ያለበት ሁኔታ መኖሩም አብራርተዉ ከተሞቻችን ወደ ተሻለ ደረጃ ከማሳደግ አንጻር ሰፊ ዉስንነት የነበረበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዉ የዞኑ መቀመጫ የሆነችዉ ወልቂጤ የእድሜዋ ያህል ከማሳደግ አንጻር ሰፊ ዉስንነት መኖሩም ጠቁመዋል።

ይህም እንደ መንግስት ጊዜ ተወስዶ ባለሀብቶችን ቀርቦ የሚቸግራቸዉን ነገር ረግዞ መስራት ያስፈልጋል ብለዉ በከተማዉ ብዙ ያልተሟሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች መኖራቸዉም አስታዉሰዉ የሰላምና የጸጥታ ችግሮች እንዳሉና እነዚህም ደረጃ በደረጃ በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

በወልቂጤ ከተማ ዛሬ ስራ በይፋ የጀመረዉ የስራኖ ሆቴል እዚህ ከተማ ላይ ከመስራት ሌላ ቦታ ላይ ቢሰራ የበለጠ አትራፊ እንደሆነም ተናግረዉ ይህ ቤተሰብ መነሻቸዉ ፣ የቤተሰባቸዉን፣ የአካባቢያቸዉ ገጽታ በመቀየር ላይ ትልቅ ስራ አንደሆነም አስበዉ ምንም የመንግስት እገዛ ሳይጠብቁ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በዞኑ መቀመጫ በሆነችዉ ወልቂጤ ከተማ ላይ አሳርፈዋል ብለዋል።

የሆቴሉ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠቱ በቀጣይም ለሌሎች ባለሀብቶች ሞዴል ስራ ሲሆን የዩሃንስ ሀይሌ ቤተሰቦችን በከተማዉ ላይ ላስቀመጡ ባለ አምስት ፎቅ ዘመናዊ ሆቴል በዞኑ አስተዳድር ስም አመስግነዋል።

ወጣቱ ባለሀብት ዩሃንስ ሀይሌ በፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት ሆቴሉ ባለ አምስት ወለል ደረጃዉን የጠበቀ መኝታ ክፍሎች ፣ ኤየር ኮንድሽን ሲስተም ፣ ሁለት መሰብሰቢያና ለሰርግ ምቹ የተደረጉ አዳራሾች ፣ በየክፍሎችም የብሮድ ባንድና ዋይፋይ አገልግሎት፣ ሁለት ባርና ሬስቱራንት እንዲሁም የካፌ አገልግሎት ፣ መመገብያ አዳራሽ እንዳሉትም ጠቁመዋል።

ሆቴሉ ስታንዳርዱን የጠበቀ ሲሆን መዋኛ ገንዳና የመዝናኛ ቦታ በቦታ ጥበት አማካኝነት ማካተት እንዳልተቻለም ተናግረዋል።

ሁሌ ሀብት ማፍራት ብቻዉን በቂ አይደለም ያሉት ወጣቱ ባለሀብት አካባቢም ማልማት ያስፈልጋል ብለዉ የጉራጌ ተወላጅ ባለሀብቶችና ከዞኑ ዉጪ ያሉ ባለሀብቶች ወደዚህ አካባቢ መጥተዉ ማልማት እንዳለባቸዉም አብራርተዋል።

ሆቴሉ የአካባቢዉ ገጽታ እንዲያጎላ ተደርጎ የተሰራና ጥራት ያለዉ አገልግሎት እንደሚሰጥም አስታዉቀዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ አሰፋ በበኩላቸዉ የሀይሌ ስራኖ ቤተሰቦች ማህበራዊ ሀላፊነት ለመወጣት ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን የአካባቢዉ ገጽታ ለመገንባት የገነቡት ሆቴል እንደሆነም ተናግረዋል።

በመንግስት በኩል መሟላት የሚገባቸዉ ቅድመ ሁኔታ ሳይሟላላቸዉ በራሳቸዉ ጥረትና ልፋት ግንባታዉን ጨርሰዉ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸዉ ሊመሰገኑ እንደሚገባም አስታዉቀዋል።

ሆቴሉ በከተማዉ መገንባቱ ገጽታ ከመገንባት በተጨማሪ ለብዙዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርና በተጨማሪ የከተማዉን ገቢ የሚያሳድግ እንደሆነም አብራርተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *