በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ ።

የኮሮና ቫይረስ የሚያሳድረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ መንግስት ለህብረተሰቡ በሽታው መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልባቸው መንገዶች ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ሀብት የማሰባሰብ ስራ ማከናወኑን የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት የቫይረሱ ስርጭት ለመግታት የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንደነበሩ የተናገሩት ኃላፊው አሁን ህብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርገው ጥንቃቄ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ በየቀኑ በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።
በቅርብ ጊዜ የተከሰተው ኦሚክሮን የተባለው የኮቪድ ወረርሽኝ በመላው አለም በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ የሚገኝ በሽታ ሲሆን የበሽታው ምልክቶች በቀላሉ ለመለየት የሚያስቸግርና በመጀመሪያ ይስተዋሉ የነበሩ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምልክቶች ላይታዩ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

አክለውም አቶ ሸምሱ መንግስት በነጻ ያቀረበው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክትባት በመከተብ በሽታው የሚያሳድረው ተጽእኖ መቋቋም ይቻላል ብለዋል።

በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በክትባቱ ላይ ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ አርመው ክትባቱን በመውሰድ ጤናቸውን ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዞኑ 275 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የክትባት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው በቀጣይ አገልግሎቱ ለሁሉም የዞኑ ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

እስካሁን ከተመረመሩት 46ሺህ 268 የህብረተሰብ ክፍሎች 2ሺህ 415 ሰዎች በኮቪድ 19 በሽታ የተያዙ ሲሆን 45 ሰዎች ህይወታቸው አጥተዋል ብለዋል።

በዞኑ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ያሉት አቶ ሸምሱ በየቀኑ እስከ 15 ሰዎችን በበሽታው ይያዛሉ። ይህ ደግሞ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚያሳድረው ተጽዕኖ የከፋ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ ሀገሪቱ የገጠማት አሁናዊ ችግር በብቃት ለመወጣት ጤናውን የተጠበቀ አምራች የሰው ኃይል ስለሚያስፈልጋት ሁሉም ሳይዘናጋ እራሱንና ወገኑን ለመጠበቅ የኮቪድ 19 ፕሮቶኮል ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ሚዲያዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በበሽታው አስከፊነት ላይ ግንዛቤ ሊፈጥሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *