በክረምት ወቅት የተጀመረዉ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በበጋዉ ወቅት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በጉራጌ ዞን ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ የ2013 የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መዝጊያና የ2014 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መክፈቻ ዝግጅት ተካሄደ።

ወጣቶች በክረምትና በበጋ ወቅቶች በበጎ ፈቃድ ስራ በመሰማራት ማህበረሰቡን የሚጠቅሙና የተለያዩ የልማት ስራዎችን ያከናዉናሉ።

በእለቱ ተገኘተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንዳሉት የ2013 የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለየት የሚያደርገው ሀገራችን ኢትዮጵያ በዉስጥና በውጭ ሀይሎች በርካታ ፈተናዎች ዉስጥ ሆና በዘርፉ አበረታች ዉጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

የዘንድሮው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዞናችን የተጀመረዉን የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ወጣቱ ከሌላ ጊዜ በተለየ ሁኔታ ጊዜውን ፣ጉልበቱንና ሀብቱን ሳይሰስት ለማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁሉንም ወጣቶች ያሳተፈና ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚዘወተር ባህል እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና የአሰራር ስርዓትን መዘርጋት ለስራው ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች እውቅና የሚያገኙበትና የሚበረታቱበት ስረአት በመዘርጋትና ባለ ሀብት ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ ማስተባበርና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዞናችን ወጣቱ በክረምት የተጀመረውን መልካም ተግባር በበጋው ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወላጆችም ሆኑ ህብረተሰቡ ወጣቶች የሀገሪቱን መፃኢ እድል የሚወስኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን በመገንዘብ በወጣቶች ላይ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት በተግባር በመቀየር ጊዜቸውን ፣ጉልበታቸውን ፣እውቀታቸውንና ሀብታቸውን በመጠቀም የተስተካከል ስብእና ተላብሰው እንዲያድጉ በዞናችን የሚገኙ ብሄረሰቦች ፣ባህሎቻቸዉና እሴቶቻቸዉን እንዲውቁና እንዲጠበቁ በማድርግ ረገድ ህብረተሰቡ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ እንዳሉት በዞናችን የሚገኙ ወጣቶች በልማት ስራዎች ተሳትፎ በማድረግና በዲሞክራሲ ስረአት ግንባታ በንቅናቄ በመሳተፍ እንደ ሀገርና እንደ ዜጋ መገለጫና ማረጋገጫ ከሆኑ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የ2013/14 የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ13 የተለያዩ ዘርፎች በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ መስተዳድሮች መከናወኑን ገልጸው በዚህም 235 ሺህ 8 መቶ 36 ወጣቶችን በማሳተፍ በዚህም 840 ሺህ 6 መቶ 2 የህብረተስብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸዉም አመላክተዋል፡፡

በጎ ፈቃድ ወጣቶች በክረምቱ ባከናወኑት የልማት ስራዎች ሊወጣ የነበረ 230 ሚሊየን 274 ሺ 7መቶ ብር ማዳን መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የ2014 የበጋ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 1መቶ 80 ሺህ 1 መቶ 88 ወጣቶችን በማሳተፍ ህግ ወጥ የሰዎች ዝውዉር መከላከል ፣የደም ልገሳ በማድረግ ፣የቀይ መስቀል አገልግሎት የመስጠት ፣የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅና የመሳሰሉትን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ላይ እንደሚያተኩሩም ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ በመድረኩም የተገኙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በክረምቱ የተሰራዉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እጅግ አበረታች ዉጤት የተመዘገበበት በመሆኑ በቀጣይም በበጋው ወራት በስፋት መከናወን እንዳለበትም አስታዉቀዋል።

በእለቱም የክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ስኬታማ እንዲሆን ያደረጉ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ባለሀብቶች እንዲሁም ወጣቶችና የሚመለከታቸዉ ሌሎች ባለድርሻ አካላቶች መሳተፋቸዉም ታዉቋል።

በመጨረሻም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሻለ ስራ ለሰሩ ተቋማትና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *