በክልሉ በተቀናጀ የበጋ ግብርና ልማት ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም በዘርፉ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።


በዞኑ ቸሃ ወረዳና እምድብር ከተማ አስተዳደር በተቀናጀ የበጋ የግብርና ልማት ስራዎችን የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ሌሎችም በተገኙበት ጉብኝት ተካሂዷል።

በጉብኝቱ የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በክልሉ 147 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ 110 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩበ ሰብል መሸፈኑንና 2ሺህ 4መቶ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ መሸፈኑን ገልጸዋል።

ክልሉ በግብርናው ዘርፍ እምቅ አቅም እንዳለው ያነሱት ኃላፊው በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ የተማሩ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ያገኙትን ድጋፍ በመጠቀም እየሰሩት ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን በመጠቀም በተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎች ወጣቱና አርሶ አደሩ በተደራጀ መንገድ እያመረቱ በመሆኑ ለወጣቱ የስራ እድል መፈጠሩ፣ ገቢ እያደገ መሆኑን፣ ገበያው እየተረጋጋ መሆኑንና በዚህም በዘርፉ ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ በተቀናጀ የበጋ ግብርና ልማት ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም በዘርፉ ርብርብ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በግብርና ዘርፍ ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የገቢ አቅም ለማሳደግ፣ የህብረተሰቡን የአመጋገብ ስርአት ለመቀየርና እንደ ሀገር ብልጽግና ለማረጋገጥ በዘርፉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዞኑ ሰፊ የሚታረስ መሬቶችን እንዲታረሱ በማድረግ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር በተሰሩ ስራዎች በዛሬው እለት በቸሃ ወረዳ በተለያየ የሙያ መስክ የተመረቁ ወጣቶች አንድ ላይ በመቀናጀት መሬት ወስደው በመስራታቸው ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በግብርናው ዘርፍ ዝናብ ብቻ ጠብቆ ውጤታማ መሆን እንደማይቻል የገለጹት አቶ ላጫ በዞኑ ያሉ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ ስራ እየተሰራ ያለው ስራ የበርካታ ወጣቶች ህይወት እየቀየረና የገቢ አቅም እያሳደገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በሌማት ቱሩፋት ዘርፍ ህብረተሰቡ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገብ በእንሰሳት ዘርፉ ወጣቶች ከመኖ ጋር በማቀናጀትና የበሽታ ቁጥጥር ስራ በማጠናከርና የተሻሻሉ ዝርያ በማርባት በወተት ልማት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች እንደሆነ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ያለው የኑሮ ውድነት ለመቀነስና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በዞኑ በግብርናው ዘርፍ ሁሉም ተቀናጅቶ በመስራት በስፋት ማምረት ይገባል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው የመስክ ጉብኝቱ አላማ በዞኑ የተቀናጀ የበጋ ግብርና ልማት ስራዎችን ውጤታማነት ለማየት እንደሆነ አመላክተዋል።

በዞኑ በመደበኛ መስኖ 24 ሺህ 290 ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱንና በዚህም 22 ሺህ 5 መቶ ሄክታር ማልማት መቻሉንም ጠቁመው በበጋ መስኖ ስንዴ 1ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 5መቶ 37 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል ብለዋል አቶ አበራ።

በዞኑ በተቀናጀ የበጋ ግብርና ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩ ህይወት በሚቀይርና የገበያ ሁኔታ ሊያረጋጋ በሚችል መልኩ የተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ያነሱት አቶ አበራ በዞኑ ያለውን ጸጋ ይበልጥ በመጠቀም በቀጣይም አጠናክሮ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዞኑ ወጣቶች በሰብል፣ በእንሰሳት ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩት ያለው ስራዎችን ሌሎችም በዘርፉ በመሰማራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ አሁን ላይ ያለውን የገበያ ሁኔታ ለማረጋጋት ይበልጥ መስራት ይገባል።

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ በዘንድሮ አመት በወረዳው በመደበኛ መስኖ 3450 ሄክታር መሬት በመሸፈን 112 በላይ በወረዳው በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈኑ አመላክተዋል።

በወረዳው በተቀናጀ የበጋ የግብርና ልማት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቅሰው ያሉ እምቅ አቅሞችን በመጠቀም በሌሎችም ቀበሌዎች ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ወጣት አቶ ዳንኤል ሺፈታ እንዳሉት በቸሃ ወረዳ 5 በመሆን በግማሽ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በመደበኛ መስኖ ስንዴ የጀመሩት ስራ አሁን ላይ 30 ሄክታር መሬት እያለሙ መሆኑና በዚህም ለ1መቶ ወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በ28 ሺህ መነሻ ካፒታል የጀመሩት ስራ አሁን ላይ 7 ሚሊዮን ብር ማደጉንም ገልጸዋል።

ወረዳው እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ በመጠቀም የተለያዩ ፍራፍሬ እያለሙ ሲሆን ያመረቱት ምርት ወደ ገበያ በማውጣት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በወረዳውና በእምድብር ከተማ ወጣቶች በእንሰሳት ዘርፍ በመስራት በቀን እስከ 1መቶ 10 ሊትር ወተት ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረው ወጣቶቹ ሌሎች ወጣቶች በዘርፉ ተደራጅተው እንዲሰሩ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በጉብኝቱም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፣ የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ ጁሃር፣ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፣ የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ ጨምሮ የዞን፣ የቸሃ ወረዳ አመራሮችና ሌሎችም ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *