በእሳት አደጋው ወድመው የነበሩ ቤቶች በአዲስ መልክ ስለተሰራላቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉን በጉራጌ ዞን ቀቤና ወረዳ የፈረጀቴ ቀበሌ በአደጋዉ ሰለባ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስታወቁ።

መስከረም 17/2015 ዓ.ም

በእሳት አደጋው ወድመው የነበሩ ቤቶች በአዲስ መልክ ስለተሰራላቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉን በጉራጌ ዞን ቀቤና ወረዳ የፈረጀቴ ቀበሌ በአደጋዉ ሰለባ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስታወቁ።

በጉራጌ ዞን ቀቤና ወረዳ ሌንጫ ቀበሌ ልዩ ስሙ ፈረጀቴ መንደር በባለፈው መጋቢት ወር በእሳት አደጋ ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች መልሶ በማቋቋም ሂደት ላይ ተሳትፎ ላበረከቱ የተለያዩ አካላት የወረዳው አስተዳደር የምስጋና፣የእውቅናና የቤቱን ርክክብ ፕሮግራም አካሂዷል።

የቀቤና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብደላ ጀማል በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ባለፈው መጋቢት ወር በሌንጫ ቀበሌ በፈረጀቴ መንደር በድንገተኛ የእሳት አደጋ ቤታቸው ለወደመባቸው አካላት ሁሉም የወረዳው ጠቅላላ አመራር ማህበረሰቡን በማሳተፍ ለተጎጂዎች ደስታ እስከ መጨረሻ ያደረገው ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ እጅጉን የሚበረታታ ነበር ብለዋል።

አመራሩ በአንድነት ተቀናጅቶ ከሰራ ሁሉንም ችግሮች መቅረፍ እንደሚቻል በተግባር የተማርንበት ነው ብለዋል።

በዚህ በጎ ተግባር ለተሳተፉ ለጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ ለደቡብ ክልል መንግስት፣ ለፌደራል ተቋማት ብሎም ከውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች ግለሰቦችና የወልቂጤ ከተማና አበሽጌ ወረዳ ፣ ለቀቤናና ለጉራጌ ልማትና ባህል ማህበራትና ሌሎችም ድጋፍ ላደረጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በዛሬ እለት የወረዳው አስተዳደር በወረዳው ህዝብ ስም አመስግነዋል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን አስተዳደር ተወካይና የዋና አስተዳዳሪ አማካሪ አቶ ፈቱ አብዶ እንደገለፁት የወረዳው መንግስት የልማት አቅሞችን በአግባቡ በማስተባበር ቤት ንብረታቸዉ በእሳት አደጋ የወደመባቸው ወገናኖቻችን መልሶ ለማቋቋም ያደረገው ሰፊ ጥረትና የህብረተሠቡ ምላሽ የሚበረታታና በቀጣይ በሌሎች ልማቶች ሊደገም እንደሚገባ አመላክተዋል።

ተጎጂ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ በመደበኛ የልማት ስራዎች በመሳተፍ እንዲችሉና በቋሚነት ወደ መደበኛ ስራቸዉ እንዲመለሱ ሊደገፉ ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

እንደ አቶ ፈቱ ገለፃ የመረዳዳትን ባህላችንን የበለጠ በማጎልበት የዞኑ ማህበረሰብ አንድነት የበለጠ በማጠናከር ዉጤታማ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።።

የቀቤና ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም በተፈጠረው አደጋ የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብድሽኩር ደሊል የአደጋው ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በወረዳው ካሉት መላው አመራር ጋር በመመካከር በዋና አስተዳዳሪ የሚመራ አብይ ኮሚቴና ከስሩ የሀብት አሰባሰብ ፣የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴዎችን በዋናነት በማዋቀር ህብረተሰቡን የማሳተፍ ስራ በስፉት መሰራቱ ገልፀዋል።

ተጎጂዎች አሁን ወዳሉበት የተረጋጋ ህይወት ለመመለስ በኮሚቴው በኩል ገቢ ተሠብስቦ ስራ ላይ የዋለ በአይነት 4 ሚሊየን 524ሺ 15 ብር፣ በጥሬ ገንዘብ 3 ሚሊየን 938ሺህ 573ብር በድምሩ 8 ሚለየን 462ሺህ 588ብር በማሰባሰብ ስራ ላይ መዋሉን ባቀረቡት ሪፖርት አመላክተዋል ።

በቀበሌዉ የአደጋዉ ሰለባ የነበሩ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት መላዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተረባርቦ የተቃጠለ ቤታቸዉ በአዲስ መልክ ስለተሰራላቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉ እና ለተደረገላቸው ድጋፍም አመሥግነዋ ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምርያ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *