በአፍሪካ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገራችን ለ33ኛ ጊዜ የትምህርት ተሳትፎ እና ጥራትን ማሳደግ ጊዜ አሁን ነዉ በሚል መሪ ቃል የአፍሪካ የህጻናት ቀን በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ሰላምበር ትምህርት ቤት በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከበረ።

በአሉን አስመልክቶ መምሪያዉ ለተለያዩ ችግር የተጋለጡ ወገኖች የዘይትና የፉርኖ ዱቄት ድጋፍ አጋርቷል።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ነጅብያ መሀመድ እንዳሉት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀት በመጠቀም ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሴቶች በማሰባሰብ ለመጽሐፍት ግዢ ማዋል ተችሏል ብለዋል።

ህጻናት በሁሉም ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑና ደህንነታቸዉን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የህጻናት አደረጃጀቶች ተዋቅረዉ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

የዞን መዋቅር ጨምሮ 16 የህጻናት ፓርላማ አደረጃጀቶች ፣ሲ አር ሲ ቴክኒክ ኮሚቴና በተለያዩ ክበባት በማሳተፍ ህጻናት ደህንነታቸዉና ተሳትፎአቸዉ ለማረጋገጥ አበክረዉ እየሰሩ እንደሆነም አመላክተዋል።

በተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ትምህርታቸዉን ያቋረጡ ተማሪዎች በመለየትና ሀብት በማሰባሰብ በተገቢዉ ድጋፍ ተደርጓል ያሉት ሀላፊዋ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህጻናት በሀገር ዉስጥ አማራጭ ድጋፍና እንክብካቤ ፕሮግራሞች ላይ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ቤተሰባቸዉ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ህጻናት ዴይኬር በማቋቋም ያለ ስጋትና ያለ ምንም ጭንቀት የመንከባከብና የመንግስት የስራ ሰአት ሳይሸራረፍ ህጻናቶች ሳይጎዱ በስራቸዉ ዉጤታማ ስራ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩም አብራርተዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን ለመደገፍ ከዞን እስከ ታችኛዉ መዋቀር ከስራ ማስኬጃ አንድ ፐርሰንት በመቁረጥ የበርካታ ህጻናት ችግር መቅረፍ እንደተቻለና ለተለያዩ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ህጻናት ተገቢዉን ፍትህ የሚያገኙበት የአንድ ማዕከል አገልግሎት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነም ተናግረዋል።

በእለቱ የተገኙት የወልቂጤ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ላምሮት በላይ እንዳሉት ህጻናት በጥሩ ስነ ምግባር ታንጸዉ እንዲያድጉ የዘንድሮ የአፍሪካ የህጻናት ቀን ትምህርት ቤት ዉስጥ ወሳኝ ነዉ።

የህጻናት ጉልበት ብዝበዛና አስገድዶ መድፈርና መሰል ችግሮች ለመቅረፍ የግንዛቤ ስራዉ በስፋት እየሰሩም እንደሆነም ተናግረዋል።

የዞኑ የህጻናት ፓርላማ ዋና አፈ ጉባኤ ህጻን አዲስ ምስጋናዉ እንዳለዉ የህጻናት መብት ለማስጠበቅ ፓርላማዉ አበክሮ እየሰራ እንደሆነም ተናግሮ ህጻናት ባህላቸዉን እንዲያዉቁ እንዲሁም ትምህርታቸዉ በተገቢዉ እየተከታተሉ መሆኑም አብራርቷል።

በእለቱም የማዕድ ድጋፍ የተደረገላቸዉ አንዳንድ ወገኖች እንዳሉት በተደረገላቸዉ የዘይትና የፉርኖ ዱቄት ድጋፍ ደስተኛ መሆነቸዉም ተናግረዋል።

በመጨረሻም ለፕሮግራሙ መሳከት ምክንያት ለሆኑ ትምህርት ቤቶችና የቃቄ ዉርደት የኪነት ቡድን አባላት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *