በአገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎች የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ የተማሪዎች አቅም መገንባት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2015 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ግማሽ አመት እቅድ አፈጸጸም አስመልክቶ የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ ።

የዞኑ ትትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እንደገለፁት ብቁና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመቅረጽ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ተቋማት ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ማጠናከር ይገባል።

የቅድመ አንደኛ ትምህርት ተማሪዎች ማስላት፣ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ መሰረት የሚጣልበት ደረጃ በመሆኑ ማዕከላቱ ማራኪ፣ ለመማር ማስተማር ስራ ተመራጭ ለማድረግና ብቃት ባላቸው መምህራን ለማደራጀት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በ2015 የትምህርት ዘመን 86 ሺህ 780 ህጻናት የቅድመ አንደኛ ትምህርት ማግኘት መቻሉን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።

በዞኑ የትምህርት ተሳትፎና ፍትሃዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት 358 ሺህ 114 ተማሪዎች መመዝገብ ቢቻልም 2ሺህ 356 ተማሪዎች ማቋረጣቸውን ተገልጿል ።

በመሆኑም በዞኑ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ ችግር በዘላቂነት ለማስቀረት የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አቶ አስከብር ተናግረዋል።

በ2014 የትምህርት ዘመን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች 50 እና ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 4 ነጥብ 8 ብቻ መሆናቸው በቀጣይ የዘርፉ ባለሙዎች እና አመራሩ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።

ተማሪዎች በአገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት በክፍል ፈተና ከሚያስመዘግቡት ውጤት አኳያ ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ የተሻለ ዝግጅት በማድረግ የተማሪዎች ውጤት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የዞኑ ማህበረሰብ የትምህርት ተቋማት በማስፋፋት ረገድ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ ቢሆንም በ12 ክፍል የተመዘገበው ውጤት እንዳስቆጫቸው ገልጸዋል።

የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል የመምህራን አቅም መጎልበትና ተነሳሽነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት ተሳታፊዎች በቀጣይ በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት መሰረት በማድረግ ተመዝነው እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለው የተማሪዎች የመጽሐፍ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

የጎልማሶች ትምህርት ለትምህርት ጥራትና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ጣቢያዎቹ ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ ከማድረግ ጎንለጎን የዘርፉ ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች፣ የዞኑ መምህራን ማህበር እንዲሁም የመምሪያው የማኔጅመንት አባላት ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *