በነዳጅ ላይ የታየውን የዋጋ ጭማሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአነስተኛና መካከለኛ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ላይ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ መደረጉም የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የታሪፍ ማሻሻያው በመመሪያው መሠረት ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተጠቁሟል ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩም ይታወቃል ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በትራንስፖርት ዋጋ ላይ የታሪፍ ጭማሪ መደረጉም ይታወቃል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ የህዝብ ትራንስፖርት አደረጃጀትና የደረጃ ብቃት ማረጋገጫ ቡድን መሪ አቶ መኮነን አመርጋ እንዳሉት በክልሉ ተጠንቶ የወረደው አዲሱ የህዝብ ትራንስፖርት የታሪፍ ማሻሻያ በአዋጅ በተሠጠው ስልጣን መሠረት የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የህዝብ ትራንስፖርት የታሪፍ ስሌትን በተከተለና ወቅታዊ የነዳጅ ዋጋ የተሽከርካሪ መለዋወጫና ልዩ ልዩ ወጪዎችን ታሣቢ በማድረግ በአነስተኛና መካከለኛ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት በሚሰጡባቸው በ153 መስመሮች ላይ ጥናት በማድረግ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ መደረጉን በቀን 04/04/2014 ዓ. ም በሳወቀዉ መሠረት ከቀን 06/042014 ዓ.ም በዞኑ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ።

ይህ የታሪፍ ጭማሪ ማሻሻያ በመደበኛነት በየሁለት ዓመቱ በክልል ደረጃ የሚጠና ማሻሻያ ሳይሆን በወቅታዊ የቅባትና ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ፣የተሽከርካሪዎች መለዋወጫና ልዩ ልዩ የተሽከርካሪ ወጪ ጭማሪን ታሳቢ በማድረግ የተደረገ ማሻሻያ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አሽከርካሪዎች ከፊት ለፊት ለተገልጋይ ግልፅ በሆነ ቦታ አዲሱን የታሪፍ ክፍያ ዋጋ እንዲለጥፉና ከመናሀሪያ ሳይወጡ ደረሰኝ በመቁረጥ ሂሳብ እንዲቀበሉ በማድረግ የህዝብ ተሽከርካሪ ማህበራትና የስምሪት ባለሞያዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ ጉልህ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ይህንን ህግ በሚተላለፍ ተሽከርካሪዎች ሲያጋጥሙ ተገልጋዩ ህብረተሰብ ህጋዊ መብቱን ተጠቅሞ ትክክለኛ መረጃ ለመንገድ ትራፊክ ፓሊስና የመንገድ ተቆጣጣሪ ባለምያዎች በመስጠት ተመጣጣኝ የዕርምት እርምጃ በመውሰድ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በማሻሻያ ጥናቱ ላይ ያልተካተቱ መስመሮች እንዳሉ የገለፁትአቶ መኮነን አመርጋ የመንገዱ ደረጃ ታሳቢ በማድረግ በጥናቱ መሠረት የሚመለከተው አካል የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚያደርግበት አስታዉቀዋል።

ኃላፊው አክለውም በዞኑ አገልግሎት ለሚሠጡ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች በአስፓልት በኪሎ ሜትር አንድ ብር ከ35 ሳንቲም የነበረውን ወደ 1 ብር ከ90 ሳንቲም ፤በፒስታ/በጠጠር/መንገድ 1 ብር ከ54 ሳንቲም የነበረውን ወደ 2 ብር ከ23 ሳንቲም የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉንም አብራርተዋል ።

አቶ ቴዎድሮስ አለማየሁ በወልቂጤ ከተማ የኦሮሚያ ኬኒሳ አነስተኛና መለስተኛ የህዝብ ባለንብረቶች ማህበር የስምሪት ኃላፊ እንደገለጹት የወቅቱን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን መነሻ በማድረግ የተሽከርካሪ ባለንብረቶችንና ተገልጋዩን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተሞከረበት አግባብ ጥሩ ነው ብለዉ በቀጣይ የተሽካሪዎች የመለዋወጫ ዋጋና ሌሎች ተያያዥነት ያለቸው የገበያ ሁኔታን ለማረጋጋት በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብሏል ።

አሁን ላይ እንደ ሀገር የተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ባለንበት ወቅት ግንባር ሄደን በመዋጋት ትልቁን መስዋዕትነት መክፈል ባንችልም እንኳን በየተሠማራንበት የስራ መሥክ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ህግን መሠረት በማድረግ በቅንነት በማገልገለ ሀገራዊ ግዴታችን ልንወጣ ይገባል ብለዋል ።

አቶ አብራር አብዶ የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪ ሲሆኑ መንግስት ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ከወቅቱ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫና የመንገዶች ምቹ አለመሆንና በሌሎች ምክንያቶች አዋጪ አለመሆኑን ገልፀው መንግስት በቀጣይ በድጋሚ ሊያየው ይገባል ብለዋል ።

እንደ መንግስት አሁን ላይ ከገጠሙን ሀገራዊ ፈተናዎች፣ በየጊዜው እየጨመረ ካለው የኑሮ ውድነትና ተደራራቢ ችግሮችን ታሳቢ አድርገን የምናነሳቸው ህጋዊ ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉት ሀገር ሰላም ስትሆን መሆኑን በመገንዘብ በየተሠማራንበት የስራ ዘርፍ ህብረተሰቡን በቅንነት በማገልገል የድርሻችን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

አሽከርካሪዎች ህብረተሠቡን ሳያማርሩ በጥሩ ስነ ምግባርና ሃላፊነት በሚሠማው መልኩ ከማገልገል አንጻር ሰፊ ጉድለቶች እንደሚስተዋሉና ይህንንም ለማስተካከል የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትል ሊያደረጉ እንደሚገባ ተናግረዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነዉ ።

= አካባቢህን ጠብቅ!
= ወደ ግንባር ዝመት!
= መከላከያን ደግፍ!

ስለ ታሪፍ ዝርዝር መረጃ በቴሌግራም ቻናላችን መመልከት ይችላሉ

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *