በትምህርት ስርዓት ላይ የተከሰተው የውጤት ስብራት በመጠገን ብቁ ተወዳዳሪና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለማፍራት እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

መምሪያው የ2016 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የተግባር አፈፃፀምና የ1ኛ ወሰነ ትምህርት ዞን አቀፍ የእርከን ማጠቃለያ ፈተና አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማሪያም እንደገለጹት በዞኑ ያጋጠመውን የትምህርት ውጤት ስብራት ለመጠገን ህብረተሰቡ፣ ባለሀብቱና መንግስት ተቀናጅተው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ስራዎች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም በትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረገው ርብርብ እስካሁን ከ191 ሚሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ በማሰባሰብ ወደ ተግባር መገባቱ አቶ መብራቴ ገልፀዋል፡፡

በአዲሱ የትምህርት ስርዓት የተዘጋጁ ከ1-6ኛ ክፍል የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሀብት ለማደባሰብ በተከናነው የህብረተሰብ ንቅናቄ እስካሁን ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ መጽሐፍቶቹን ለማሳተም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱን የተናገሩት ኃላፊው የ2016 የትምህርት ዘመን ዞን አቀፍ የእርከን ማጠቃለያ ፈተና ከጥር 27/2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡

የክልሉ የሳይንስና የሂሳብ ትምህርት ክህሎት ልዕቀት ማዕከል ባዘጋጀው የፈጠራ ስራዎች ውድድር ላይ ዞኑን ወክለው እንዲሳተፉ የተለዩ አራት ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ በመቻላቸው በፌደራል ሳይንስና ሂሳብ ትምህርት ውድድር ላይ ተሳተፉ በፌደራል ውድድርም አራቱም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው እውቅና ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡

ተማሪዎችም ከእምድበር 2ኛ ደረጃ፣ ከወልቂጤ ከተማ ህዳሴ ፍሬና አበሩስ 2ኛ ደረጃና ከአገና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የተመለመሉ ሲሆን ከእነዚህም አንዱ ተማሪ በቀጣይም በሀገር አቀፍ Steam Power ፕሮግራም ላይ በወልቂጤ ዩንቭርስቲ ታቅፎ ለተሻለ የፈጠራ ስራ ድጋፍ እንዲደረግለት እድል ማግኘቱን አቶ መብራቴ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ መብራቴ ገለጻ በዞኑ በ341 ጣቢያዎች ላይ ለተማሪዎች በጉራጊኛ ትምህርት እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መደረጉ የትምህርት አቀባበላቸው በማሳደግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይረዳቸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የዞኑ ህዝብ በማሳተፍ የትምህርት መሰረተ ልማት በማሟላት የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ የተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባር ለማሻሻል የሚደረገው ርብርብ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በቀጣይ የመምህራን እጥረት መቅረፍ፣ የተማሪ መጠነ ማቋረጥ መቀነስ፣ የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍት ማቅረብ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *