ዩኒየኑ 9ኛው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤው በወልቂጤ ከተማ አካሄደ፡፡
በጉራጌ ዞን ከሚገኙ ዩኒየኖች አንዱ አግኖት ኃላፊነቱ የተወሰነ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ዩኒየን ሲሆን በስሩ 306 መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ይገኛሉ፡፡
የጉራጌ ዞን ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት ወንባርጋ እንደገለፁት መንግስት የብዝሀ ሀብትና አቅም በማደራጀት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራ ሲሆን መሰረታዊ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት በአሰራር ፣ በሰው ሀይል፣ በቁሳቁስና በአደረጃጀት እንዲዘምኑ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል፡፡
የዞኑ ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤትም ህብረተሰቡ በቁጠባ፣ በሸማቾች፣ በቤቶች እና በሌሎች መሰረታዊ ህብረት ስራ አደረጃጀቶች እና ህብረት ስራ ዩኒየኖች በማደራጀት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ምህረት ገልፀዋል።
እንደ አቶ ምህረት ገለፃ በተቋማት የሚስተዋለው የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ አግኖት የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ዩኒየን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ሲሆን ዩኒየኑ የብድር አገልግሎት በመስጠት የዜጎች የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል አድርጓል፡፡
የዩኒየኑ የቁጠባና የብድር አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ ቀልጣፋና ጥራት ያለው በመሆኑ በየጊዜው ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
ዜጎች ከተቋሙ በሚያገኙት የብድር አገልግሎት በመጠቀም ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች የስራ እድል ለመፍጠር አስችሏቸዋል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ዩኒየኑ የላቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
የአግኖት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ግንባሩ ተክሌ ዩኒየኑ በዞኑ በሚገኙ በ10 ወረዳዎችና በ5 ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በቀቤና ልዩ ወረዳ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የቁጠባ መጠን ለማሳደግ እና በብድር አጠቃቀም ላይ በተለያዩ ቦታዎች ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፈጠሩ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ቁጠባ የተሰበሰበ ሲሆን ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማሰራጨት እንደተቻለ አቶ ግንባሩ ተናግረዋል፡፡
የህብረተሰቡ የብድር ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ የተናገሩት ስራ አስኪያጁ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለሚሰማሩ ወገኖች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የቁጠባ መጠን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዩኒየኑ ካሉት 103 ሺህ 802 የተናጠል አባላት 66 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ያላቸው ጠንካራ የቁጠባ ባህልና የብድር አጠቃቀም ስርዓት ዩኒየኑ ይበልጥ ስኬታማ እንዳደረገው አቶ ግንባሩ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የነበሩ ሴቶች በተፈጠረላቸው የብድር አገልግሎት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል በመፍጠር አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የዩኒየኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ እንዳለ አለሙ በከተማና በገጠር የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሰማሩ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ከመቅረጽ አልፎ በገንዘብ አያያዝ፣ አጠቃቀም ላይ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል።
ከመፍረስ የሰውን ህይወት በኑሮ ደረጃ መቀየር የቻለው አግኖት በርካቶች ከድህነት ጎዳና አውጥቶ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
አቶ ይርጋ ንዳ የአበሽጌ ወረዳ የመንግስት ሰራተኞች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር አባል ሲሆኑ ወ/ሮ አለም ደረግ በእዣ ወረዳ ስመሙ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር አባል ናቸው፡፡
እንደ አባላቱ ገለፃ በህብረት ስራ ማህበር ከተደራጁ ወዲህ ባገኙት የብድር አገልግሎት ተግተው በመስራታቸው በኑሯቸው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ችለዋል፡፡
ዩኒየኑ ቁጠባ ባህሉን ያደረገ ማህበረሰብ ለመፍጠር እያደረገ ያለው እንቅሰቃሴ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አባላቱ ወጣቶች፣ ሴቶችና ህፃናት በገንዘብ ቁጠባ ላይ በማሳተፍ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡