በቀጣይ በዞኑ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉ ድርሻ መወጣት እንዳለበት የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።


በዞኑ የሚሰጠው ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥና በቀጣይ ተግባራቶች ላይ ለዞኑ ትምህርት መምሪያ እንዲሁም ለትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ባለሙያዎች ኦረንቴሽን ተሰጥቷል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማርያም እንደገለፁት በቀጣይ በዞኑ የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉ ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሰላም እስኪ ጠናቀቅ እንዲሁም ተማሪዎች ያለ እንግልት እና ተረጋግተው እንዲፈተኑ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉ አስታውቀዋል።

ከዚህ በፊት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እና የገጠሙ ችግሮችን በመለየት ስራው ውጤታማ እንዲሆን ባለሙያው በኃላፊነት፣በቁርጠኝነትና በተጠያቂነት እሳቤ እንዲሰራ መክረዋል።

አቶ መብራቴ አክለውም የተቀመጡ ህጎች ተግባራዊ እንዲሆን የግንዛቤ ስራዎችን የበለጠ መስራት፣ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት መስጠት እንዲሁም ከተሽከርካሪና ከሰአት አጠቃቀም ጋር የሚታዩ ክፍተቶች ትኩረት ተደርጎ ሊሰራባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

9ሺ 4መቶ 88 ተማሪዎች በወልቂጤ ዩኒቨርስቲና በዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ተመድበው ሀገር አቀፍ የዩኒቨርስቲ መግብያ ፈተና የሚወስዱ ሲሆን ተማሪዎችም የተቀመጡ መመሪያዎችን በአግባቡ በመተግበር ፈተናውን ተረጋግተው እንዲወስዱ መልእክት አስተላልፏል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር እንዳሉት ስራው በስኬት ለማጠናቀቅ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ “ፍተሻ ከመነሻ”በሚል አሳቤ በመነሳት ተማሪዎች በነጻነት ተጉዘው ፤ ተረጋግተው ተፈትነው፣በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የትምህርት፣የትራንስፖርትና መንገድ እንዲሁም የሰላምና ጸጥታው መዋቅር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ተማሪዎችም ምንም አይነት የትራንስፖርት እንግልት እንዳይገጥማቸው ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር መምሪያው በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

አቶ ሙራድ አክለውም ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ ለሚጓዙ ተማሪዎች የትራንስፖርት ክፍያ በመንግስት የሚሸፈን ሲሆን ከዚያ በታች ለሆኑት ደግሞ ተማሪዎች በግላቸው እንደሚሸፍኑ አስገንዝበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አካላት እንደገለጹት ከዚህ በፊት የነበሩ ጥሩ ልምዶች ማስቀጠልና በተለይ ተማሪዎች ፈተናው ተረጋግተው እንዲፈተኑ የግንዛቤ ስራን አስቀድሞ በመስራት ችግሮች ሲገጥሙ በአፋጣኝ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

አክለውም ተቀናጅቶ መስራት፣የሚመደቡ አሽከርካሪዎች ጥራት ያላቸውና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም ለተማሪዎች በጥሩ ስነ ምግባር የሚያጓጉዙ ሊሆኑ እንደሚገባ አስታውቀው ፈተናው በስኬት ለማጠናቀቅ የተሰጣቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *