በስነጽሁፍ የዕድሜ ዘመን ተሸላሚ ፤ ሃያሲ፣ ደራሲ እና ተርጓሚ የክብር ዶክተር ሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያም የምስጋና ስነስርዓትና በደራሲው የተዘጋጀ ‹‹የሺንጋ መንደር›› የተሰኘ መጽሃፍ ርክክብ መርሀ ግብር በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የታደሙት የዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት ካውንስል አባላት፤ከዞን ትምህርት መምሪያ የተውጣጡ የትምህርት ባለሙያዎች፤ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንና ከአባ ፍራንሷ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተውጣጡ 50 ተማሪዎች ሲሆኑ በዕለቱም በፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ ገብሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደገለጹት የሃያሲ፣ ደራሲ እና ተርጓሚ የክብር ዶክተር ሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያም መወድስ እና የመጽሃፍ ርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙ እንግዶችን በማመስገን እኚህን ታላቅ የጥበብ ሰው ዛሬ ልናከብራቸው፤በስነጽሁፍ ዘርፍ ላበረከቱት ትልቅ አስተዋጽኦ ክብርና ሞገስ ልንሰጣቸው፤የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን በታላቅ አድናቆት ልንዘክር፤በዕድሜ ዘመናቸው ያስረከቡንን ደማቅ የጥበብ አሻራ ለትውልድ እንዲሻገር መሰረት ልንጥል፤ ለተተኪው ትውልድ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉልን ስንጋብዝ ፍቅራችንን ገልጸን የጻፉትን ‹‹የሺንጋ መንደር›› የተሰኘ በጉራጊኛ እና በአማርኛ የተጻፈ መጽሀፍ 1000 ቅጂ ዩኒቨርሲቲው በግዢ ተረክቦ በየትምህርት ቤቱ ለሚገኙ የነገው ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች በመለገስ እንዲጠቀሙበትና ተተኪ ትውልዶችም የታላቁን ደራሲ የህይወት ተሞክሮዎችን በመቅሰም ተማሪዎቹ በቀጣይ ስኬታማ ህይወት እንዲኖራቸው በማሰብ ጭምር መሆኑን ዶክተር ዮሀንስ ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ዮሀንስ አያይዘውም ሲገልጹ ‹‹የሺንጋ መንደር›› የተሰኘው መጽሀፍ ከ60 ዓመት በፊት የተጻፈ መሆኑን አስታውሰው ደራሲው ባለፉት የዕድሜ ዘመናቸው 8 የራሳቸው የሆነ ወጥ ስራቸውንና 8 የትርጉም ስራቸውን ለታዳሚ ማቅረባቸውን አስታውሰው በህይወት ከቀሩልንና ከምንሳሳላቸው ብርቅይ የኢትዮጵያ ደራሲያን መካከል አንዱ መሆናቸውን፤ የኢትዮጵያው “ማክሲም ጎርኪ” ፤”ዊሊያም ሼክስፒር” በሚል መጠሪያ የሚወደሱ፤ከዓለም ደራሲያን ዝርዝር ውስጥ ከታዋቂው ኢትዮጵያዊ ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ጋር አብሮ ስማቸው የሚዘከር፤በጉራጊኛ (ለመጀመሪያ ጊዜ)፤በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች በመጻፍ ላለፉት ስልሳ ዓመታት በድርሰቱ ዓለም የቆዩ፤ከታላላቆቹ ጥበበኞች ከደራሲ ስብሀት ገ/እግዚአብሄርና ከተስፋዬ ገሰሰ ጋር ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አብረው የተማሩ ፤ በ1990ዎቹ በሀገራችን ተካሒዶ በነበረው የሽልማት መርሐ-ግብር ላይ በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የዕድሜ ዘመን ተሸላሚ በሆኑበት ወቅት ስብሀት ገ/እግዚአብሄር “ለተገቢው ሰው የተሰጠ ተገቢ ሽልማት” ሲል ለነበራቸው የስነጽሁፍ ሁለንተናዊ ብቃት በኩራት የመሰከረላቸው፤ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲም በ2007 ዓም ደራሲው በስነጽሁፉ ዘርፍ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያበረከቱትን ስነጽሁፋዊ አስተጽኦ ከግምት በማስገባት የክብር ዶክትሬት የሰጣቸው መሆኑን በዝርዝር አስታውሰዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ክፍሌ ሌንቴሮ በበኩላቸው የሰው ልጅ እውቀትን ፍለጋ ምን ያክል እንደሚታትር፤ እንደሚጥርና እንደሚተጋ ሃያሲ፣ ደራሲ እና ተርጓሚ የክብር ዶክተር ሳህለ ስላሴ ብርሃነማርያም ማሳያ መሆናቸውን ገልጸው ይህንን የካበተ ልምዳቸውን ፤ዘመን የማይሽረው ስራቸውን ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያሻግሩ በማሰብ በዚሁ አጋጣሚ ተሳታፊ ተማሪዎችም የእኚህን ታላቅ የስነጽሁፍ አባት ፈለግ በመከተል የህይወት ጉዞዋቸውን እንዲያሳኩ በማሰብ በተለይም የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢ የሆኑት ተማሪዎች ለዚህ መድረክ በተለየ ሁኔታ መጋበዛቸውን ገልጸዋል፡፡

የክብር ዶ/ር ሳህለስላሴ ብርሃነ ማርያም ለአንባቢ ካበረከቷቸው ስራዎች መካከል ‘እምዩ’፣ ‘እምቢ ባዮች’፣ ‘የሁለት ከተሞች ወግ’ እና ‘መከረኞች’ በተሰኙ ታላላቅ የትርጉም ሥራዎቻቸው ይታወቃሉ፡፡ ‘የሺንጋ መንደር’ ወይም ‘የሺንጋ ቃያ’ የተሰኘው የጉራጊኛ ቋንቋ ልቦለድ የበኩር ሥራቸው ሲሆን ‘ባሻ ቅጣው’፣ ‘ሹክታ’፣ ‘The Afersata’ እና ‘Warrior King’ እንዲሁ ካበረከቷቸው መጻሕፍት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ሃያሲ፣ ደራሲ እና ተርጓሚ በሆኑት በክቡር ዶክተር ሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያም በ1959 ዓ.ም በጉራጊኛ ቋንቋ የታተመው እና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተተረጎመው ‘የሺንጋ መንደር’ ወይም ‘የሺንጋ ቃያ’ የተሰኘው ልቦለድ መጽሃፍ የአማርኛ ትርጉም በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ ያሉ ትምህርት ቤቶች በቤተመጽሀፍ በማስቀመጥ እንዲገለገሉበትና ልምድ እንዲቀስሙበት በማሰብ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በኩል ለየትምህርት ቤቶቹ እንዲከፋፈል ተደርጓል፡፡

እጅግ የተከበሩ የክብር ዶክተር ሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያም በሀገራችን የትርጉምና የድርሰት ስራ ባልተስፋፋበት ዘመን ለስነጽሁፍ ዕድገት፤ ለንባብ ክህሎት ማደግና መዳበር፤ሀገራቸውን በውጭው ዓለም በማስጠራት፤ለባህልና ቋንቋ ዕድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዕውቅና ሰረተፍኬትና በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀላቸውን ልዩ ሽልማት በክብር አበርክቶላቸዋል፡፡

የክብር ዶ/ር ሳህለስላሴ ብርሃነ ማርያም የሀገር ዋርካ፤ባለምጡቅ ስብዕና ፤የዕውቀት ምሰሶ፤ማንበብ ሙሉ ሰው ያደረጋቸው፤መጽሃፍ ያጀገናቸው፤ ተቀድቶ የማያልቅ የዕውቀት ውቅያኖስ የሆኑ፤በህይወት ያሉ ቤተመጽሀፍ መሆናቸውን ደፍሮ የሚያስነግርና ተነግሮ የማያልቅ የዕውቀት ጎርፍ የሆኑ፤ጊዜን በእቅድ ለክተው በትግበራ ሰፍተው የሚጠቀሙ፤ የዕውቀትን ዳና በመከተል ዋጋ የከፈሉና በከፈሉትም ዋጋ አብዝተው ያተረፉ፤ለሚጽፏቸው መጻሕፍት የፍልስፍና መሠረት እንዲኖራቸው ያደረጉ፤ለዚህ ዓለም ያላቸውን አዎንታዊ አመለካከት ለአንባቢዎቻቸው ለማሳየት በእጅጉ የጣሩ፤በፖለቲካ ሳይንስ ተመርቀው በአንጻሩ ግን በስነጽሁፍ የተመረቁ ያህል በስነጽሁፉ ዓለም ውስጥ እንደፈለጉ የተምነሸነሹ፤የህይወት ልምዳቸው በራሱ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ የሆነ፤ የአንድ ብዙ የሆኑ፤ ለሀገርና ለህዝብ ወርቅ የሆነ ስነጽሁፍን ያበረከቱ፤ለመልካም ዘር የተከፈተ ልብ ያላቸው፤የማስተዋላቸው ርቀት የመረዳታቸው ጥልቀት ለጉድ የሚያሰኝ፤ የጸሀፊያን ቁንጮ ብንላቸው የሚያንስባቸው የሀገር ባለውለታ ናቸው፡፡ የእኚህን የሀገር ባለውለታ የስነጽሁፍ አባት ስራ መዘከር መታደል ብቻ ሳይሆን መመረጥም ነው፡፡ ረጅም ዕድሜን ከሙሉ ጤንነት ጋር ተመኘን።
መረጃው የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *