በስርዓተ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰተው የህፃናት መቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡

ቀን 26/1/2015 ዓ.ም

በስርዓተ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰተው የህፃናት መቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡

የጉራጌ ባህልና ልማት ማህበር ከጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ጋር በመቀናጀት በስርዓተ ምግብ አስፈላጊነት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጉራጌ ባህልና ልማት ማህበር ዳሬክተር አቶ ቅባቱ ተሰማ በዞኑ የሚስተዋለው የስረዓተ ምግብ ችግር አሳሳቢነት ለመከላከል የእንስሳትና የእጽዋት ተዋጽኦዎች መጠቀም አለብን ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ቅባቱ ገለፃ በስርዓተ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰተው የህፃናት መቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ጉልባማ ከባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ባለፉት ዓመታት ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጋላጭ የነበሩ ህፃናትና ነፍሰጡር እናቶች ህይወት ለመታደግ የተሰሩ ስራዎች አበረታች እንደነበሩ አቶ ቅባቱ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ባለድርሻ አካላት የህፃናት መቀንጨር ችግር ለመቅረፍ የሚያደርጉት ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግና የተጣለባቸው ኃፊነት በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል የውይይት መድረኩ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ማህበሩ ከተለያዩ ድርጅቶች ፣ከዞንና ከወረዳዎች ጋር በመቀናጀት በስርዓተ ምግብ ሲሰራ እንደነበር የገለጹት የጉልባማ ዳይሬክተር አቶ ቅባቱ ተሰማ ማህበሩ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ ራይት ቱ ግሮው/ Right 2 grow/ የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት በዞኑ በ6 ወረዳዎች በምግብና ስነ ምግብ ላይ በርካታ ስራዎች ሰርቷል ብለዋል፡፡

ይህንን ተግባር በማጠናከር በስርዓተ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚቀነጭሩ ህጻናት ቁጥር ለመቀነስ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የዞኑ ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ አብዱላዚዝ ሹሜ በበኩላቸው የውይይት መድረኩ በስርዓተ ምግብ አቅርቦት ላይ የነበሩ ክፍተቶች ለመሙላት ከማስቻል በተጨማሪ ብቁ አዕምሮ ያለው ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ርብርብ የላቀ ተሳትፎ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ በስርዓተ ምግብ እና በተቋማት የስርዓተ ምግብ ተወካዮች ተግባርና ሃላፊነት በሚመለከት ሁለት ሰነዶች በዞኑ ጤና መምሪያ የስርዓተ ምግብ ባለሙያ በአቶ አንዳአምላክ ወልዴ የራይት ቱ ግሮው/ Right 2 grow ግብረሰናይ ድርጅት አስተባባሪ በአቶ መኮነን ታምሩ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የራይት ቱ ግሮው/ Right 2 grow ግብረሰናይ ድርጅት አስተባባሪ በአቶ መኮነን ታምሩ በዞኑ በ6 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ በ18 ቀበሌዎች የህጻናት መቀንጨር ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል፡፡

እንደ አቶ መኮነን ገለፃ ህብረተሰቡ በስርዓተ ምግብ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ ለማጠናከር ለ29 ሺህ 612 የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል፡፡

በ18 ቀበሌዎች ለ3 ሺህ 281 ህፃናት የእድገት ክትትል የተደረገላቸው ሲሆን 7ሺህ 51 ህፃናት የቫይታሚን ኤ እንዲሁም 46 ነፍሰጡር እናቶች የተመጣጠነ ምግብ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡

አክለውም አስተባባሪው ለስርዓተ ምግብና ለንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እጥረት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየት ለ35 የውኃ ተቋማት ጥገና ማድረግ የተቻለ ሲሆን 3ሺህ 417 አባወራዎች በጓሮ አትክልት እንዲሁም አንድ ሺህ 957 አባወራዎች በእንስሳት ተዋጽኦ ተጠቃሚ ማድግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የዞኑ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ፣የዞኑ የስረዓት ምግብ ተወካዮች እንዲሁም ራይት ቱ ግሮው የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት የሚሰራባቸው የጌታ፣የምሁርና አክሊል፣ የአበሽጌ፣ የገ/ጉ/ወለኔ፣ የቸሀ እና የእንደጋኝ ወረዳዎች የእናቶችና ህፃናት አስተባባሪዎችና የልማት ዕቅድ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ሲል ዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *