በምክር ቤት የጸደቀውን በጀት በማስተዳደርና የሀብት ቁጥጥር በማድረግ ለዞኑ ህዝብ ልማት እንዲውል በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ የ10 ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዶ ሀሰን በመድረኩ ላይ እንዳሉት በምክር ቤት የጸደቀውን በጀት ለተቋማት ከተከፋፈለ በኋላ በአግባቡ በማስተዳደርና የሀብት ቁጥጥር በማድረግ ለዞኑ ህዝብ ልማት እንዲውል እየተሰራ ነው፡፡

ከበጀት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም በዞኑ አብዛኛው ወረዳዎችንና ከተማ አስተዳደሮች የጥሬ ብር እጥረት እየገጠማቸው ደመወዝ በብድር ይከፍሉ እንደነበር አስታውሰው በዚህ አመት ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተሰራው ስራ ባለፉት 11 ወራት ከእንደጋኝ ወረዳ በስተቀር የጥሬ ብር ብድር በማስቀረት መቻሉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ወረዳዎች የውስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅማቸው በማደጉ፣ ከ2007 አስከ 2015 አመተ ምህረት ያደሩ የአፈር ማዳበሪያ እዳዎችን ኦዲት በማድረግ 51 ሚሊዮን የኦዲት ጉድለት ማግኘት የተቻለ ሲሆን ከዚህ ወስጥ 76 ከመቶ የሚሆነውን ማስመለስ መቻሉንና በየተቋማቱ ተከማችተው የሚገኙ የማያስፈልጉ ንብረቶች በማስወገድ ገቢ በማግኘታቸው የጥሬ ብር እጥረት መቅረፍ መቻሉን አቶ አብዶ አስገንዝበዋል፡፡

በተያያዘ በዞኑ በርካታ ተቋማት ኦዲት ተደርገው 21 ሚሊዮን ብር ጉድለት የተገኘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 83 ከመቶ የሚሆነው የኦዲት ግኝት ማስመለስ እንደተቻለ ኃላፊው አክለዋል፡፡

የ2016 በጀት ዓመት የዞኑ ጥቅል በጀት 4 ቢሊዮን 57 ሚሊዮን ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 50 ነጥብ 5 ከመቶ ሚሆነውን በጀት በዞኑ የውስጥ ገቢ መሸፈን መቻሉን የገለጹት አቶ አብዶ በቀጣይ ዓመት ዞኑ የሚያመነጨው ሀብት በአግባቡ በመሰብሰብ ገቢ የማሳደግ ስራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በልዩ ትኩረት ይሰራል፡፡

በቀጣይ በሁሉም መዋቅር ላይ ለደመወዝ የሚያዘው በጀት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ከሰው ሀይል ጋር በማነጻጸር ኦዲት ማድረግ፣ የበጀት አመቱ የሂሳብ ሪፖርት እስከ ሰኔ 30/2016 መዝጋት፣ የገቢ ሽፋን ማሳደግ፣ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ የመንግስት ንብረቶች አሟጦ (በሽያጭ፣ በስጦታና በመቅበር) ማስወገድ እና የኦዲት ጥራትና ተደራሽነት ማሳደግ ላይ ርብርብ እንዲደረግባቸው አቶ አብዶ አሳስበዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ የበጀትና ሲቪክ ትብብር ዘርፍና ምክትል የመምሪያ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ አለሙ እንደገለጹት በዚህ ዓመት የበጀት አጠቃቀም የተሻለ በመሆኑ የሰራተኞች ደመወዝ ያለምንም ችግር መክፈል መቻሉንና በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡

የደመወዝ ወጪ ከፍ ያለባቸው መዋቅሮች በትክክል ስራ ላይ ያሉ ሰራተኞች እየተከፈለ ስለመሆኑ ክትትል የማድረግ ስራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ የመንግስት ፋይናንስ ዘርፍና ምክትል የመምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሊም ሸምሱ በበኩላቸው የገቢና የፋይናነስ ተቋማት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የውስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅማቸው ለማሳደግ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የሚወጡ ወጪዎች ክፍያ ቅድሚያ ለሰብዓዊ ጉዳዮች መሆን እንዳለበትና በቀጣይ በወጪ ቅነሳ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ሳሊም ተቁመዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በየአካባቢያቸው የሚመነጨው ሀብት አሟጦ በመሰብሰብ የገቢ አቅም ለማሳደግ፣ የኦዲት ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግና የሰው ሀይል ኦዲት የማድረግ ስራ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *