በምርምር ማዕከል ውጤታማነታቸውን የተረጋገጡ የግብርና የምርምር ውጤቶችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲቱዩት የወልቂጤ የግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡

በወልቂጤ የግብርና ምርምር ማዕከል እየተከናወኑ የሚገኙ የምርምር ስራዎችን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጉራጌ ዞን ቸሃና አበሽጌ ወረዳዎች የመስክ ጉብኝት ተካሄደ፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲቱዩት የወልቂጤ የግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቤቴል ነክር በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት የምርምር ማዕከሉ የተቋቋመው ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ የዞኑ አርሶ አደር ተጠቃሚ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በምርምር ማዕከሉ ምርጥ ዘር ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ኑግ፣ በቆሎ፣ ቦለቄን ጨምሮ 91 የምርምር ስራዎችን ውጤታማነታቸውን ተረጋግጦ ለአርሶ አደር ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ቤቴል ነክር ተናግረዋል፡፡

አሲዳማ መሬት በኖራ ለማከም ከ3 ሺህ ኩታል በላይ ኖራ በማቅረብ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻላቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ለ1 ሺህ 6 መቶ 43 አርሶ አደሮች የብዜት ዘር በመስጠት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ክፍለማሪያም መኩሪያ በጉብኝቱን ወቅት እንደገለጹት ባለፉት አምስት አመታት አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀምና በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እንዲያለማ በማድረግ ምርትና ምርታማነቱን በማሻሻል ተጠቃሚ እንዲሆን በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

የወልቂጤ የግብርና የምርምር ማዕከል ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ጋር በመቀናጀት በበቆሎ፣ በስንዴ፣ በጤፍ ሰብሎች አርሶ አደሩ ከማደራጀት ጀምሮ ምርጥ ዘርና የክሎት ስልጠና በመስጠት ሰፋፊ የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በሰፊው የማላመድ ስራ እየሰራ መሆኑን አቶ ክፍለማሪም መኩሪያ ተናግረዋል፡፡

በወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ያዕቆብ በበኩላቸው በዘንድሮ አመት በሰብል፣ በዘር ብዜት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በእንስሳት ጨምሮ በ1 መቶ 18 የምርምር ሙከራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ምርምር እያካሄዱ በሚገኙበት በቤራዠ ንዑስ ጣቢያ የአካባቢ ዝርያዎች በመሬቱ አሲዳማ በመሆኑ ምክንያት ምርት የማይሰጡበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ከአካባቢው እየወጡ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ ያዕቆብ የምርምር ስራው ሲጠናቀቅ ለአርሶ አደሩ አማራጭ ዘር ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመስክ ጉብኝቱ ወቅት አግኝተን ካነጋገርናቸው ተጠቃሚ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አብድራሂም ፈርሁ እና አቶ አብዶ አሺቃ ይገኙበታል። ሁለቱም በሰጡት አስተያየት የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል ባደረገላቸው የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ የአረም ቁጥጥር ማድረጊያ የኬሚካል ድጋፍ ተጠቅመው በኩታ ገጠም ማሳ በ70 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ በማምረት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በምርት ዘመኑ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።
በወልቂጤ የግብርና ምርምር ማዕከል እየተከናወኑ የሚገኙ የምርምር ስራዎችን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጉራጌ ዞን ቸሃና አበሽጌ ወረዳዎች የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *