የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለጹት በዞኑ በ2016/2017 የመኸር ወቅት ከ103 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቋሚና በሥራ ሥር ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል።
በልማቱም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል ኩታ ገጠም አሰራርን ጨምሮ ለግብርና ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ነው የገለጹት።
በዞኑ በመኸር ወቅት ከለማው ከ103 ሺህ በላይ ሄክታር ማሳ ከ50ሺህ በላይ ሄክታሩ በኩታገጠም መልማቱንና ምርታማነትን የሚጨምሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
ይህም አርሶ አደሮች ጉልበታቸውን አስተባብረው ሥራቸውን በተቀናጀ መንገድ በመፈጸም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብለዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በመኸር እርሻ ከለማው ማሳ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግም ምርጥ ዘር በወቅቱ ከማቅረብ ጀምሮ ለኩታ ገጠም የግብርና ልማት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፣ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ክትትልና ድጋፍ በማድረጋቸው ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየቱን ተናግረዋል።
በተለይም በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ አርሶ አደሮች በቅንጅት መስራታቸው የተሻለ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ነው የገለጹት።
በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ የአዘርና ሲሰ ቀበሌ አርሶ አደር ሀብቴ ቶማስ “ከዚህ ቀደም በባህር ዛፍ ተሸፍኖ የነበረውን መሬት በጤፍ፣ በቆሎና በሽንብራ ማልማት ከጀመርኩ ወዲህ የተሻለ ተጠቃሚ ሆኛለሁ” ብለዋል።
በግል ከሚያለሙት በተጨማሪ በ60 ሄክታር መሬት ላይ ከ30 አርሶ አደሮች ጋር ጤፍ በኩታገጠም እያለሙ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን መተግበራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በምርታማነትና በኑሯቸው ላይ ለውጥ ለማምጣት እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር ሸሚም ናስር በበኩላቸው ከባህላዊው የአስተራረስ ዘዴ ወጥተው ማሳቸውን በኩታ ገጠም ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነታቸው እያደገ መምጠቱን ነው የተናገሩት።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብርና ሥራ የሚያስገኘውን ውጤት የተረዱ ወጣት ልጆቻቸውም በግብርና ሥራቸው ውጤት እያስመዘገቡ መምጣታቸውን ገልፀዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።