በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት በቡታጅራ ከተማ በተካሄደው የባህልና ልዩልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የተሳተፈው የጉራጌ ዞን ልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።


በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት በቡታጅራ ከተማ በተካሄደው የባህልና ልዩልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የተሳተፈው የጉራጌ ዞን ልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።

በቀጣይ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች ላይ የሚመዘገበው ውጤት ለማሻሻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ለልዑካን ቡድኑ የምስጋና ፕሮግራም በተዘጋጀበት መድረክ ላይ እንደገለጹት በአንደኛው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ልዩልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ልዑካን ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት አስደሳች ነው።
ዞኑን የወከለው ልዑካን ቡድን በሰፊ የሜዳልያ ልዩነት በቀዳሚነት ማጠናቀቁ አበረታች መሆኑ የገለጹት አቶ ላጫ በቀጣይ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች ላይ በመሰማራት የተሻለ ውጤት ከማስመዝገብ በተጨማሪ ሀገሪቱን የሚወክሉ ስፖርተኞች ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በዚህ ውድድር የተመዘገበው ውጤት ትልቅ መነቃቃት የሚፈጥር በመሆኑ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋይሰል ሀሰን ዞኑን የወከለው ልዑካን ቡድን በብቃትና በስነምግባር ያሳየው ተሳትፎ እና ያስመዘገበው ውጤት አበረታች እንደሆነ አስረድተዋል።

ለዚህ ውጤት የዞኑ አስተዳደር ፣ አበባው ሰለሞን ኮንስትራክሽንና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ያበረከቱት አስተዋጽኦ በጉልህ እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ውድድሮች 81 ሜዳሊያዎች መገኘታቸው አስደሳች ነው ያሉት አቶ ፋይሰል በዚህ ውድድር የተመዘገበው ውጤት እንደሚያሳየው በዘርፉ በደንብ ከተሰራ ዞኑ በአለም መድረክ ደምቀው የሚታዩ የበርካታ ስፖርተኞች መፍለቂያ መሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ልዑካን ቡድኑ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት እንዲችል አስተዋጽኦ ላበረከቱ እና ለልዑካን ቡድኑ ንቁ ተሳትፎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ለልዑካን ቡድኑ የምስጋናና የምሳ ግብዣ መርሀግብር በወልቂጤ ከተማ ጆካ ሆቴል ተካሄዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *