በማህበረሰቡና በአከባቢው ተወላጅ ባለሀብቶች ተሳትፎ በተያዘው በጀት አመት ከ1 መቶ 20 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመንገድ ልማት እየተሰራ እንደሆነ የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ አስታወቀ ።

የአከባቢውን ማህበረሰብና ተወላጅ ባለሀብቱን በማስተባበር ቀበሌን ከዋና መንገድ የሚያገናኝ መንገድ በመሰራቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞን ነዋሪዎች ተናገሩ ።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት በ 2015 ዓ.ም በማህበረሰብ ተሳትፎ ከ 120 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ህብረተሰቡን የመንገድ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በህብረተሰብ ተሳትፎ በ45 ሚሊየን ብር ወጪ የ1መቶ 7 ኪሎ ሜትር መንገድ የአፈር ጥርጊያና የ88 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠጠር የማልበስ ስራ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ተሠርቷል ብለዋል ።

በህብረተሠብ ተሳተፎ ቀበሌን ከቀበሌና ከወረዳ እንዲሁም ከዋና መንገድ ጋር የሚያገናኝ በጉመር ፣በሶዶ ፣በቸሀ ፣በእኖር መገር ወረዳና በሌሎችም ወረዳዎች መሰራቱን አቶ ሙራድ ከድር ገልጸዋል ።

መንግስት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ባለድርሻ አካላትንና መምሪያው ያሉትን አቅሞች በአግባቡ በመጠቀም ማህበረሰቡን የመንገድ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ኃላፊው በተለይም ህብረተሰቡንና የአከባቢው ተወላጅ ባለሀብቶችን በመንገድ ልማቱ የማሳተፍ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።

አቶ ታምራት ሀብታሙ በቸሀ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽፈት ቤት የህበረተሰብ ተሳትፎ ቡድን መሪ ሲሆኑ በ2015ዓ.ም ግማሽ ዓመትየአካባቢው ማህበረሰብ ተወላጅ ባለሀብቶችን በማስተባበር የ19.5 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ገልፀዋል ።

የሶዶ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽፈት ቤት የህበረተሰብ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ታምሬ ወልደሰንበት በበኩላቸው ያካባቢው ህረተሰቡንና ተወላጅ ባለሀብቱን በማስተባበር አራት ቀበሌዎችን የሚያገናኘው የገሪኖ እንሰት ተክል 7 ኪሎ ሜትር እና ሌሎች በርካታ ቀበሌዎችን ከዋና መንገድ የሚያገናኝ የ20 ኪሎ ሜትር መንገድ ባለፉት 6 ወራት መከናወኑን ገልፀዋል።

ከነጋገርናቸው መካከል የሶዶ ወረዳየገሪኖ እንሰት ተክል ቀበሌ ነዋሪ ብዙነህ ለሚ እና በቸሀ ወረዳ የቦራገራ ቀበሌ ኗሪ ደጀኔ ግርማ ሁለቱም በሰጡት አስተያየት ቀበሌያቸውን ከዋና መንገድ የሚያገናኝ መንገድ ባለመኖሩ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ሲጋለጡ እንደነበረ ተናግረዋል።

አሁን የአከባቢውን ማህበረሰብና ተወላጅ ባለሀብቱን በማስተባበር ቀበሌያቸው ከዋና መንገድ የሚያገናኝ መንገድ በመስራቱ የነበረባቸው ችግሮች መቀረፉን አብራርተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *