በመኸር እርሻ የሚጠብቁትን ምርት ማግኘት እንዲችሉ የሰብል እንክብካቤና የአረም ቁጥጥር ተግባራቸውን አጠናክረዉ እያከናወኑ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ።

ጳጉሜ 05/2014

በመኸር እርሻ የሚጠብቁትን ምርት ማግኘት እንዲችሉ የሰብል እንክብካቤና የአረም ቁጥጥር ተግባራቸውን አጠናክረዉ እያከናወኑ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ።

በሰብል እንክብካቤና የአረም ቁጥጥር ማነስ ምክንያት ምርት እንዳይቀንስ አስፈላጊው ግብዓት በወቅቱ እንዲደርስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

አርሶአደር ተባረክ በደዊ፣ አይሻ ጀማልና ሀብታሙ ምትኩ በወረዳው የዳርቻ ቀበሌ አርሶ አደሮች ሲሆኑ በመኸር እርሻ ወቅት የዘሩትን ሰብል በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አረምና ተባይ በሰብል እድገት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የቤተሰቦቻቸው ጉልበትና በደቦ ሆነው የአረም ቁጥጥር ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እንደ አርሶአደሮቹ ገለጻ እንክብካቤ ያልተለየው ማሳ ከፍተኛ ምርት የሚያስገኝ በመሆኑ የባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ተቀብለው እየሰሩ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት በሚፈልጉት መጠን ባለማግኘታቸው ተጽእኖ ቢያሳድርባቸውም ያገኙትን የግብዓት አማራጭ በመጠቀም ማሳዎቻቸውን በሰብል መሸፈን ችለዋል።

የግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሮች ወቅቱን በጠበቀ ሁኔታ ሰብልን መንከባከብና የአረም ቁጥጥር ማድረግ እንዲችሉ ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም ሁሉም አርሶ አደሮች የቤተሰቦቻቸው ጉልበት በመጠቀምና በደቦ በመስራት ምርትና ምርታማነታቸው ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አቶ ዘውዱ ዱላ የእዣ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ሲሆኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት 5ሺህ 800 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ 5ሺህ 670 ሄክታር መሬት በጤፍ፣ በገብስ፣ በአተር፣ በባቄላና በሌሎችም ሰብሎች መሸፈን ተችሏል ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ በወረዳው በመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው 5ሺህ 673 ሄክታር መሬት 181 ሺህ 536 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ይገኛል።

በሰብል እንክብካቤና በአረም ቁጥጥር ማነስ ምክንያት ምርት እንዳይቀንስ አስፈላጊው ግብዓት እንዲቀርብላቸው ተደርጓል።

በመሆኑም ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ለማድረግ 3ሺህ 689 ኤን ፒ ኤስ እና 1ሺህ 249 ኩንታል ዩሪያ ማዳበሪያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

በሰብል እንክብካቤ እና በመዳበሪያ እጥረት ምክንያት የምርት መቀነስ እንዳይከሰት አርሶ አደሩ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማሳውን በአግባቡ በመንከባከብ ከፍጆታው አልፎ ለገበያ ማቅረብ እንዲችል መስራት እንደሚጠበቅበት አቶ ዘውዱ ተናግረዋል።

አያይዘውም ኃላፊው በተያዘው የመኸር ወቅት የፍራፍሬ መንደር ለመመስረት 96 ሺህ የተለያዩ ችግኞች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *