በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ የሠለጠነ በቁ የሠው ኃይል በጥራት በማፍራት ወደ ኢንደስትሪ ለሚደረገው ሽግግር የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ድርሻ የጎላ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳድር አስታወቀ።

የቡታጀራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ7ወራት እቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ከቦርድ አመራር አባላት ጋር በቡታጀራ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የኮሌጁ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለፁት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ፈቺ የሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠርና ማሻሻል የሚችሉ በመካከኛና በዝቅተኛ ደረጃ የሠለጠነ ዜጋን በማፍራት እንደሀገር ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ ሽግግር ለሚደረገው ጉዞ የጎላ ነው ብለዋል።

የቡታጀራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የካይዘን ጥራት ስራ አመራር ተግባራዊ በማድረግ በተቋሙ ያለ አግባብ ይባክን የነበረ ጊዜ ፣ጉልበትና ወጪ ለማዳን የተሰራው ስራ በሌሎች ተቋማተ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በወይይቱ ኮሌጁ የውስጥ ገቢ ከማሳደግና ሌሎቾ በአፈፃፀም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ሁሉም የቦርድ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጣ በውይይቱ የተሻለ መግባባት መፈጠሩን ገልፀዋል ።

የጉራጌ ዞን ቴክኒክና ሙያ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱ አህመድ በበኩላቸዉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተለያዩ የስልጠና ዘርፎች ብቃት ያላው የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል በአፈፃፀም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት የቦርድ አመራር አባላትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኮሌጁን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ባመቻቸው ዕድል በመጠቀም ግምታቸው 38 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የአይሲቲ መሠረተ ልማት ቂሳቁሶች ዝርጋታ በመፈፀም ወደ ተግባር መገባቱ የገለፁት አቶ አብዱ ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር የጀመራቸው መልካም የትብብር ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ የገበያ ፍላጎት መሠረት ያደረገ አጫጭር ስልጠዎች ላይ ትኩረት የማድረግና ከፍተኛ የሠልጣኝ ችግር ያለባቸውን በክላስተሩ ስር ለሚገኙ የቆሼና ቡኢ ኮሌጆች በተሻለ መልኩ የማብቃት ስራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

የቡታጀሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አብድል ዋሂድ መሀመድ እንደገለጹት ኮሌጁ የሰለጠነ የሰዉ ሀይል በማፍራት ረገድ የተጣለበትን ኃላፊነት በተሻለመልኩ በመወጣት በቀጣይ የቴክኒክና ሙያ ሳታላይት ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ እንደሆነ ገለፀዋል።

ኮሌጁ የአካባቢው ማህበረሰብ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ የዶሮመኖ ማቀነባበሪያ ፣የቆሎ መፈልፈያ ፣ በሪሞት የሚሰራ ስታብላይዘር ፣የቲማቲም ደረጃ ማውጫ ማሽንና ሌሎችም ውጤታማነታቸውን የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ወደ ተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል ።

ኮሌጁ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት በዘንድሮ ደረጃ በ350 ብር በላይ ወጪ ለአረጋውያንና የአቅመ ደካማ ቤት የመገንባት፣ 50 ተማሪዎችን የትምህርት ቁሳቁስና ሌሎች ወጪዎችን
የመሸፈንና የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር 500ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ስራ አየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ አብድል ዋሂድ ሌሎችም በርካታ የበጎ ፈቃድ ስራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ኮሌጁ ካለው የካበተ ልምድ በመጠቀምና እስካሁን ያሰመዘገባቸውን ስኬቶችን የበለጠ በማጠናከር በቀጣይ በተሻለ መልኩ ህበረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በኮሌጁ ያለውን የካበተ ልምድና ያሰመዘገባቸውን መልካም ተሞክሮዎች በሌሎች ኮሌጆች ማስፋትና በክላስተሩ የሚገኙ ኮሌጆች በተገቢዉ መደገፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

በመጨረሻም የኮሌጁ የቦርድ አመራር አባላትና የኮሌጁ ማኔጅመንት፣ የአውቶሞቲቭ፣ የህፃናት ማቆያ፣ በኮሌጁ የተዘጋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጎብኝተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *