በመንገድ ልማት ዘርፍ የጀመርነው ስራ በሌሎችም የልማት ስራዎች ላይ አጠናክረን እንሰራለን ሲሉ በእኖር ወረዳ በመንገድ ልማት ስራ የተሰማሩ የአካባቢው ተወላጆች ገለጹ።


የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት የባለሀብቱና የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝነት እንዳለው የእኖር ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት አስታወቀ።

የእኖር ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ኑርጋ እንዳሉት ወረዳው በተለይ በቡናና ጫት አምራች ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ ሲሆን እነዚህ ምርቶች ወደ ገበያ ለማቅረብ መንገድ ለወረዳው እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ገልጸዋል።

በመሆኑም የወረዳው መንግስት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊው በጀት በመመደብና ግሬደር አመቻችቶ ከህብረተሰቡ በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

በወረዳው ያሉ ቀበሌዎች ሁሉም በመንገድ ለማስተሳሰርና የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት የባለሀብቱና የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝነት እንዳለው አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።

በዘንድሮ አመት 64 ነጥብ 8 መንገድ የአፈር ጥርጊያ መደረጉ የገለጹት ኃላፊው 28 ኪሎ ሜትር ጠጠር ተደፍቷል ያሉት ኃላፊው ከ27 ሚሊየን ብር በላይ በመንገድ ግንባታ ወጪ የተደረገ ሲሆን ህብረተሰቡ ከአባቶቻችን የወረሰው መንገድ መስራትና የመጠበቅ ባህሉ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

አቶ ትግስቱ ብርሀኑና አቶ አሰፋ ቢረዳ በእኖር ወረዳ የከረቤድ ቀበሌ የኬርዲቸ ተወላጅ ሲሆኑ ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው መንገድ ባለመኖሩ በሀዘንም በደስታ ጊዜ ወደ ሰፈራቸው በሚገቡበት ወቅት በመንገዱ ብልሽት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ በከተማና በገጠር ያሉ ተወላጆች ገንዘብ በማዋጣት በመንደራቸው እስከ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ 2 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር መንገድ ማሰራታቸው ገልጸዋል።

መንገዱ ተሰርቶ በማየታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው አክለዋል።

በመንገድ ልማት ዘርፍ የጀመርነው ስራ በሌሎችም የልማት ስራዎች ላይ አጠናክረን እንሰራለን ያሉት ተወላጆቹ የአካባቢው ወጣትና አርሶ አደር ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመስኖ፣የውሃ፣የትምህርት ቤት ግንባታ እና የመብራት ዝርጋታ ፕሮጀክቶች ለማስገባት አቅደን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን ብለዋል።

አክለውም አካባቢን ማልማት ሀገር ማልማት በመሆኑ የጉራጌ ተወላጆች ወደ አካባቢያቸው በማየት መሰል አይነት የልማት ስራዎች እንዲሰሩ መልእክታቸው አስተላልፏል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *