በህጻናት ላይ አየተከሰቱ ያሉ የጉልበት ብዝበዛ፣ የኃይል ጥቃትና ህገ ወጥ ዝዉዉር አሳሳቢ በመሆኑ ሁሉም በባለቤትነት በመንቀሳቀስ ማስቆም እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።


ፍቅር እንክብካቤ ለሁሉም ህጻናት በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረዉ የአፍሪካ ህጻናት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በሰዉ ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ለተፈናቀሉ ለ270 ወገኖች የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ህጻናት በእድሜ ለጋ ሲሆኑ ህይወታቸዉን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮችና አደጋዎች ይገጥማቸዋል።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ አመተረዉፍ ሁሴን በእለቱ ተገኝተዉ እንዳሉት የአንድ ሀገር የፖለተካና የኢኮኖሚ ስርአት እድገትና የማህበረሰብ ደህንነትና ልማት ከሚመዘገብባቸዉ መለኪያዎች አንዱ የወደፊት ተተኪ ትዉልድ ለሚሆኑ ህጻናት በሚሰጠዉ አገልግሎትና እንክብካቤ ነዉ።

ህጻናት በእድሜ ለጋ ሲሆኑ ህይወታቸዉን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮችና አደጋዎች የሚገጥማቸዉ እንደሆነና ከዚህም ባለፈ ለሰዉ ሰራሽና ለተፈጥሮ ረደጋዎች ተጋላጭ እንደሆኑም አመላክተዋል።

የህጻናት መብት ፣ ደህንነት ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አስረድተዉ የህጻናት ፓርላማ አደረጃጀት በማጠናከር የሚደርስባቸዉ ጉልበት ብዝበዛ ፣ የሀይል ጥቃትና ህገወጥ ዝዉዉር ማስቀረት እንደሚገባም አብራርተዋል።

በሰዉ ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ለተፈናቀሉ ለ270 ወገኖች የምግብ ፣የንጽህናና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉም አመላክተዉ ይህንንም ድጋፍ ያደረጉ ግሎባል ዱቄት ፋብሪካ ፣ለዞኑ ቀይ መስቀል ማህበር የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለአቤም ፕሮሞሽንና ለመምሪያዎች አጠቃላይ ሰራተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህፃናት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮአርሺያ አህመድ በበኩላቸዉ የህፃናት መብትና ደህንነታቸው ተጠብቆ ጤናማና ስብዕናቸው የተሟላ ሆኖ እንዲያድጉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል ።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ብሎም እንደ ዞናችን በህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችና ወንጀሎች በአይነትም ሆነ በመጠን እጅግ እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሆነም አመላክተዋል።

የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል በየደረጃው የሚመለከታቸው የመንንግስት ተቋማት እንዲሁም የእምነት አባቶችና የባህል ሽማግሌዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስታዉቀዋል።

የጉራጌ ዞን ህፃናት ፓርላማ ዋና አፈ ጉባኤ ህፃን አዱሱ ምስጋና እንዳለዉ የጉራጌ ዞን ህፃናት ፓርላማ ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ መብቶቻቸው እንዲጠበቅ ፣የትምህርት እድል እንዲያገኙ ፣ ሌሎች የህፃናት መብቶች እንዲጠበቁና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።

የዛሬዎቹን ህፃናት መጠበቅና መንከባከብ ሀገርን እንደመጠበቅ ነዉ ብለዉ ለዚህም ስኬት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርቧል።

በመድረኩ የተገኙ አንዳንድ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ኢሰብአዊ ድርጊቶች የመከላከል ተግባር ላይ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዱወጣና የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አብራርተዋል።

በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት ለተለያዩ ማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ህፃናትና ሴቶች ድጋፍ እንክብካቤ በማድረግ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በጋራ መገንባት እንደሚገባምአመላክተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *