በህገወጥ መንገድ የተመዘበረ የህዝብና የመንግስት ሀብት ለማስመለስ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የጉራጌ ዞን ምክርቤት የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ኃይል አሳሰበ።


ግብረሀይሉ የእስካሁን አፈጻጸም ግምገማ እንዲሁም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አካሄደ።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤና የግብረሀይሉ ሰብሳቢ ክብርት ልክነሽ ስርገማ የመንግስትና የህዝብ ገንዘብ ከግለሰብ ወደ መንግስት ካዝና ለማስመለስ የተጀመረው እንቅስቃሴ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

እስካሁን በተደረጉ በኦዲት የተገኘ ገንዘብ እና ውዝፍ የማዳበሪያ እዳ የማስመለስ ሥራዎች ላይ እየመጣ ያለው ለዉጥ ጥሩ ቢሆንም በተቀመጠው ልክ እየተመለሰ ስላልሆነ በኦዲት የተገኘው ገንዘብና ውዝፍ እዳ ለማስመለስ ባለድርሸ አካላት ኃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገባ ክብርት አፈጉባኤ ወ/ሮ ልክነሽ አስረድተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በተያዘው ዕቅድ መሠረት የጠራ መረጃዎችን በመያዝ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅብናል ያሉት ክብርት አፈጉባኤዋ በቀሪ ጊዜያት የሚሰሩ ስራዎች በዉጤት በማስደገፍ የሚታይ ለዉጥ ለማምጣት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ አፈጉባዋ በአጽንኦት ገልጸዋል ።

በኦዲት ግኝት የተገኘ የህዝብ ሀብት ለማስመለስ የተለያዩ ስልቶች በመጠቀም አስመላሽ ግብረ ሀይሉ ተቀናጅቶ የማስመለስ ስራው ማጠናከር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በምክርቤቱ የኢኮኖሚ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኑርአህመድ አለዊ የ9 ወራት የቴክኒክ ኮሚቴ ሪፖርት ለኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረሀይል ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት እስካሁን ከ36 ሚሊዮን 594 ሺህ ብር በላይ የአፈር ማዳበሪያ ውዝፍ እዳ የተመለሰ ሲሆን ቀሪ ከ14 ሚሊዮን 58 ሺህ ብር በላይ አለመመለሱን ገልጸዋል።

ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በዞን ማዕከል፣ በወረዳዎች፣ በከተሞችና በክልል ተቋማት ከተገኘው ከ25 ሚሊዮን 853 ሺህ ብር በላይ የኦዲት ግኝት 20 ሚሊዮን 243 ሺህ 891 ብር ማስመለስ መቻሉ አቶ ኑርአህመድ ገልጸዋል።

በግብርና፣ በጤና፣ በገቢዎች ባለስልጣን፣ በስራ እድል ፈጠራ ተቋማት ላይ የተገኘው የኦዲት ግኝት ለማስመለስ የተሰራው ስራ አበረታች ቢሆንም ቀሪ ጉድለቶች ማሟላት ይገባል ብለዋል።

የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ ሀይል ኮሚቴዎች በበኩላቸው በሀብት አስተዳደር ስርአታችን ላይ የሚስተዋሉ የግብአት ብድር አመላለስ፤ የታክስ አስተዳደር የኦዲት ግኝት፤ የፋይናንስ የጥሬ ገንዘብና ንብረት አስተዳደር፤ በእዳ ምክንያት ከወረዳዎች የሚቆረጠው በጀት አሰባሰብና አጠቃቀም እና ለወጣቶች የተሰራጨው ብድር አመላለስና ስርጭት ችግሮች ሊቀረፉ ይገባል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *