በህብረተሰብ፣ ባለሀብትና በመንግስት ተሳትፎ አበረታች የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

መበእዣ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት በወረዳው በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎች ጉብኝት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ተካሂዷል።

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘዉዱ ዱላ በልማት ስራ ጉብኝት ወቅት እንደገለጹት በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርናና በመሰረተ ልማት የተለያዩ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

ወረዳው ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሆን የሚያስችሉ የአካባቢው ሰላም መጠበቅ፣ ለአዲስ አበባ ቅርብ መሆኑ፣ መብራት፣ ውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶች የተሟሉ በመሆናቸው ምክንያት በርካታ ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ በመምጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በውሃ ማሸግ፣ በአበባ ልማት፣ በችቡድና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኝ የብረት ፋብሪካን ጨምሮ ከ43 በላይ ትላልቅ የኢንቨስትመንት አይነቶች በልማት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠራቸውም ባለፈ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲሰበሰብ አስችለዋል፡፡

የእዣ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ከድጃ ተማም የልማት ስራ ጉብኝቱን አስመልክተው እንደተናገሩት በወረዳው የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን መረጃ ለህብረተሰቡ በመስጠት አውቆዋቸው የባለቤትነት ስሜት ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡

በልማት ስራ ጉብኝቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ በመሆናቸው በወረዳው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ፈጥነው ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ የሆኑትንና ያልሆኑትን በመለየት አስፋላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችላቸው መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

በወረዳው ከሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች መካከል አቶ ፈቃዱ አንቂየ በጓሮዋቸው የልማት ስራ ጉብኝት ሲካሄድ እንደተናገሩት ንብ በማነብ፣ በቡናና በእንስሳት መኖ ልማት ከራስ ፍጆታ ያለፈ ትርፍ ምርት በማምረት በሚያገኙት ገቢ የተሻለ ኑሮ እየኖሩ ናቸው፡፡

በቀጣይም የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ የወረዳ የግብርና ባለሙያዎችና የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች የልማት ስራቸውን በመጎብኘት እንደሚያበረታትዋቸውና ልምዳቸውንም ለአካባቢው አርሶ አደሮች እንደሚያካፍሉ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በልማት ስራ ጉብኝቱ ሲሳተፉ ካገኘናቸው ባለድርሻ አካላት መካከል አቶ ደሳለኝ አስፋው በሰጡት አስተያየት በወረዳው የሚከናወኑ በርካታ ከዚህ ቀደም የማያውቁዋቸው የልማት ስራዎች እንዳሉ መመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በእዣ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያካተተ የልማት ስራ ጉብኝት የሞዴል አርሶ አደር ማሳ፣ የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የችቡድ ፋብሪካ፣ የቲናው አበባ ልማት፣ የዳርቻ ጤና ጣቢያና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኝ የብረት ፋብሪካ ላይ ተካሂዷል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *