በሀገራችን ላይ የተደቀነው አደጋ ለመመከትና የአካባቢያችን ሰላም ለመጠበቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተገቢ ማስተግበር እንደሚገባ የዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል ገለፀ።

በዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም ዞናዊ የጸጥታ ግብር- ኃይል እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ሰነድ ዕቅድ ያቀረቡት የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ መስፍን ተካ እንዳሉት በሀገር ህልዉናና ሉአላዊነት ላይ የተደቀነዉን አደጋ ለመመከት የወጣዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 መሰረት በዞኑ የጸጥታ ስጋቶችን በብቃት ለመከላከልና እንደ ሀገርም እንደ ዞንም የተደቀነብን የሽብርተኛዉን እንቅስቃሴን ለመመከትና በመቀልበስ ሀገርን ማዳን ይገባል ብለዋል።

በየደረጃዉ የፖለቲካና የጸጥታ አመራሮች ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝርዝር አፈጻጸምና ስለወቅታዊ ሀገራዊና ዞናዊ ሁኔታ ግንዛቤ ጨብጦ ህብረተሰቡ ተደራጅቶ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢዊን እንዲጠብቅና ለሀገራዊ ተልዕኮ በህዝባዊ አደረጃጀት ዝግጁ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።

የጸጥታ ችግር በተከሰተባቸዉ ቦታዎች ሁሉ የችግሩ ምንጭም ሆነ በዉድመት ተግባርም የሚሳተፈዉ ሰላም የሚፈልግና ሰላማዊ ትግል የሚያደርግ አካል ሳይሆን የሰላማዊ ህዝብ ጥያቄና ፍላጎት ደጋፊ መስሎ ድብቅ አጀንዳቸዉን የሚፈጽሙ ሀይሎች መሆናቸዉ ችግሩ በየጊዜዉ ሲገመገም መጥቷል ብለዋል።

ከማህበራዊ ሚዲያ አንጻር በዞናችን ባለፉት ወቅቶችም ሆነ አሁናዊ ሁኔታ ዉስጥ ከአዉንታዊ ይልቅ አሉታዊ ጎኑ ይበዛል ያሉት ኃላፊዉ በየአካባቢዉ የሀሰት መረጃ እንደ እዉነተኛ ምንጭ አድርገዉ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩም ቁጥራቸዉ ቀላል እንዳልሆነም አስረድተዋል።

ሽብርተኛዉ ትህነግ በከፈተዉ ጦርነት በአማራ፣ በአፋር፣ በተላላኪዉ ሸኔ በኦሮሚያ ክልልና በክልላችን ብሎም በዞናችን አጎራባች አካባቢዎች በሰዉ ህይወት በአካልና በንብረት ላይ አረሜንያዊና እጅግ ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላበት ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ህዝቡን ዉዥንብር ዉስጥ የሚከቱና የአካባቢዉ ሰላም በሚነሱ እንዲሁም ግጭት የሚያስከተሉ መረጃዎች ቀድሞ ማምከን እንደሚገባ ገልፀው እነዚህም አካላቶች ከድርጊታቸዉ ሊታቀቡ እንደሚገባና ካልሆነ እርምጃ እንደሚወሰድባቸዉም ተገልጿል።

በዞኑ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝዉዉርና የኮንትሮባንድ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እንደሆነና እንዲሁም በሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች በማህበረሰቡ ኑሮ ላይ የዋጋ ንረት በመፍጠር ሰዉ ሰራሽ እጥረት እንዲኖር በማድረግ ተግባር ላይ የተሰማሩ ስግብግብ ነጋዴዎች የሚፈጥሩትን ችግሮች ለመከላከል ጥረት የተደረገ ቢሆንም በመሰረታዊነት ለዉጥ ማምጣት አልተቻለም ብለዋል ።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የጸጥታዉ መዋቅር በየደረጃዉ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዘርፉ ላይ እየተፈጸመ ያለዉ ሸፍጥ ህዝቡን ወደ ምሬት በማስገባት በመንግስት እምነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ቁልፍ የጥፋት ስልት በመሆኑ በየደረጃዉ ተፈትሾ ሊታረም ይገባል ብለዋል።

ሁሉም ሰዉ ለጸጥታዉ መዋቅሩ ወይም ለአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ በየአካባቢያቸዉ ለጸጥታ ስጋት የሆኑ ሰዎች በመጠቆም አካባቢው መጠበቅ አለበት ብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች ቤታቸውም ጨምሮ ለፍተሻ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸዉም አስረድተዋል።

በአገር ላይ የተፈጠረዉን ችግር ለመታደግ ሁሉም የዞኑ ማህበረሰብ ሀገር የምታደርገዉ ጥሪ ተቀብሎ መዝመትና አካባቢዉን በንቃት መጠበቅና ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበትም አብራርተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት ህብረተሰቡ በእጁ የያዘዉን የጦር መሳሪያዉ በመንግስት ጥሪ መሰረት ማሰረከብ ግዴታ መሆኑ መገንዘብ አለበት ብለዋል።

ነገር ግን ጥሪው ተከትሎ ካላስመዘገበ በመንግስት እንደሚወረስና እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል።

በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላቶች እንዳሉት መንግስት በአሸባሪዉ ቡድን ሴራና ተንኮል ሀገር እንዳትፈርስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ተገቢ ነዉ።

አሁን የተጀመረዉን መንገድ የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠልና ህብረተሰቡ የአካባቢዉ ሰላም በመጠበቅ እንዲሁም ለጸጥታ ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮችና የሚያገኛቸዉ ጸጉረ ልዉጥ ሰዎች ለህግ አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *