በሀገሪቱ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የምግብ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንደሚሰሩ በጉራጌ ዞን በተለያዩ የስራ ዘርፎች በልማት ቡድን የተደራጁ ሴቶች ገለጹ።


የሴቶች የልማት ቡድን አደረጃጀት የሴቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው እንዳሳደገላቸው የዞኑ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

አሁን ላይ በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለዉን የኑሮ ዉድነትና በተለያዩ ምርቶች ላይ የሚስተዋለዉን የዋጋ ግሽበት ለማስቀረት የሴቶች የልማት ቡድን አደረጃጀት በተሰማሩበት የግብርና ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ዉጤት ማምጣት ይኖርባቸዋል።

ወይዘሮ ኮከቤ ታደሰ እና ወይዘሮ ዝናሽ ኤጀርሶ በሶዶ ወረዳ በሴቶች የልማት ቡድን በመደራጀት ስንዴ በማምረት በአርአያነት የሚጠቀሱ ሴት ሞዴል አርሶአደሮች ናቸው።

እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ በየአደረጃጀታቸው በቁጠባ ምንነትና አስፈላጊነት ላይ በሚያደርጉት ውይይት ስለ ቁጠባ ያላቸውን ግንዛቤና የቁጠባ ባህላቸዉም እየጨመረ መሆኑም አመላክተዋል ።

በመሆኑም የቆጠቡትን ገንዘብ ተጨማሪ ሀብት እንዲያስገኝላቸው በስንዴ ምርት መሰማራታቸውን የተናገሩት እነዚህ ሴት የልማት አርበኞች በሀገሪቱ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና መንግስት ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገባቸው የምግብ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ተግተው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

አርሶ አደሮቹ አክለውም አደረጃጀቶቻቸው በህይወት ክህሎት፣ በአኗኗር ዘዬ እና በቁጠባ አስፈላጊነትና በስነ ምግብ የላቀ ግንዛቤ እንዳስገኘላቸው አብራርተዋል።

ወይዘሮ አመቱላ ጀማል የምሁር አክሊል ወረዳ አርሶአደር ሲሆኑ ወይዘሮ ሲቲ ሀይደር የቀቤና ወረዳ አርሶአደር ናቸው። እነዚህ ሴቶች ጤፍ በማምረት ከምግብ ፍጆታቸው ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የገቢ አቅማቸው ማሳደግ እንደቻሉም ገልጸዋል።

መንግስት የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ ያለው ተግባር መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ የወል መሬት እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና ጸረ ተባይ ኬሚካል በወቅቱ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

በዞኑ በልማት ቡድን የተደራጁ እነዚህ የልማት አርበኞች መንግስት እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ አድንቀው በቀጣይ በአመት ከአንድ ጊዜ በላይ ማምረት እንዲችሉ የመስኖ ውሃ፣ የኮምባይነር፣ ምርቶቻቸው ወደ ገበያ ለማድረስ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ እንደተናገሩት የሴቶች የልማት ቡድን አደረጃጀት የሴቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው ለማሳደግ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑአደረጃጀቶቹ እንዲጠናከሩ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል።

ሴቶች በልማት ቡድን በመደራጀታቸው ያላቸውን ጠንካራ የስራ ባህል ለማጎልበትና የቁጠባ ስርዓት ለማሻሻል የሚያስችላቸው በመሆኑ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲላቀቁ አስችሏቸዋል።

ሴቶች በአደረጃጀቶቻቸው አማካይነት በሚያገኙት ልምድ በጋራ ከመስራት በተጨማሪ በአነስተኛ የመስኖ ስራና በዶሮ እርባታ በመሰማራት በኑሯቸው ላይ ተጨባጭ ውጤት ያመጡ ሴቶች መኖራቸው ኃላፊዋ ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ የሴቶች የልማት ቡድን አደረጃጀት ይበልጥ ለማጠናከር በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች ስትሪንግ ኮሚቴ የተቋቋመ ቢሆንም ወጥነት ባለው አኳኋን ከመደገፍና ክትትል ከማድረግ አንጻር የሚስተዋሉ ውስንነቶች ለመቅረፍ ከመቼዉም ጊዜ በላይ አጽዕኖት ተሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።

በልማት ቡድን በመደራጀት ከዞኑ አልፎ በሀገሪቱ ብሎም በአህጉረ አፍሪካ በሞዴልነት የሚጠቀሱ የሴቶች የልማት ቡድን አደረጃጀቶች እንደነበሩ የገለጹት ወይዘሮ መሰረት የእነዚህ ሞዴል አደረጃጀት ተሞክሮ ቀምሮ በማስፋት ሴቶች በኢኮኖሚው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

=አካባቢህን ጠብቅ!
= ወደ ግንባር ዝመት!
= መከላከያን ደግፍ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGv

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *