ሴቶች እና ወጣቶች በግብርናው ዘርፍ በማሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

መበአበሽጌ ወረዳ በሴቶችና ወጣቶች የለሙ የመደበኛ መስኖ እና የበጋ መስኖ ስንዴ ማሳዎች በዞኑና በወረዳው የስራ ኃላፊዎች መጎብቱንም ተመልክቷል።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት የዞኑ ማህበረሰብ በመስኖ ስራ ያለው ተሳትፎ እያደገ ሲሆን በበጀት አመቱ ከ55 ሺህ 599 በላይ ሄክታር መሬት በመደበኛና በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት ተችሏል።

በዞኑ በመደበኛና በበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ የአበሽጌ ወረዳ ሲሆን ሴቶችና ወጣቶች በዘርፉ በማሰማራት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን አቶ አበራ ገልጸዋል።

አርሶአደሮች በመደበኛ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ እና በበልግ ወቅት እርሻ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ዞኑ ከክልሉ እና ፌደራል መንግስት ጋር በመሆን የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ እንዲቀርብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የተሻለ እና ለሌሎች አርሶአደሮች አርአያነት ያለው ተግባር ለሚያከናውኑ አርሶአደሮች እንደሚያበረታታ የተናገሩት አቶ አበራ በወረዳው በመደበኛ መስኖ በመሰማራት ውጤታማ ለሆነው ለወጣት መላኩ ተካ የውሃ መሳቢያ ጀነሬተር በስጦታ ተበርክቶለታል ብለዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ብርሃኔ በ2015 ዓም ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች አርሶአደሮች በመደበኛና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በመደራጀት በኩታገጠም እንዲያለሙ መደረጉ ገልጸዋል።

በ2014 ዓም በመደበኛና በበጋ መስኖ ስንዴ የተገኘው ምርት አበረታች እንደነበር የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው የወረዳው አርሶአደሮች ምርትና ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግና የግብዓት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ወረዳው በግብርና እድገት መርሀግብር ( AGP) እንዲታቀፍ መደረጉንም አውስተዋል።
የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘመተ አይፎክሩ በበጀት አመቱ የመደበኛ መስኖና የበጋ መስኖ ስንዴ በብዛትና በጥራት በማምረት ለገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በ2014 አርሶአደሮች በበጋ መስኖ ስንዴ ላይ የነበረባቸው የአመለካከት ክፍተት በመሙላት የተገኘው ውጠት አበረታች ሲሆን በዚህ አመት በዘርፉ የተሻለ ስራ መስራት መቻሉን አቶ ዘመተ አብራርተዋል።

የዞኑ እና የክልል መንግስት የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ቢያደርጉም ከአርሶአደሮች የማልማት አቅም አኳያ በቂ እንዳልነበር የተናገሩት ኃላፊው ወረዳው ያለውን አቅም ተጠቅሞ እንዲሟላ ከማድረግ ጎንለጎን አርሶአደሮች ተጨማሪ ግብዓት የማግኛ አማራጮች እንዲጠቀሙ ተደርጓል ብለዋል።

አክለውም አቶ ዘመተ አርሶአደሮች ከመስኖ ቀጥሎ የበልግ ወቅት እርሻ የሚጀምሩበት ወቅት በመሆኑ የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲቀርብላቸው ባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ወጣት መላኩ ተካ በወረዳው የሰሪቴና ቦቀታ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን በመደበኛ መስኖ ተሰማርቷል።

እንደወጣት መላኩ ገለጻ የግብርና ስራ ውጤታማ ለማድረግ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ከራስ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያስገኛል።

የግብርና ባለሙያዎች ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ አስረስ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትክ እያደረጉላቸው የሚገኙ ሲሆን በቀጣይም የተሻለ ምርት ለማምረት ግብዓት በወቅቱ ማቅረብ ይገባል ብሏል ወጣት መላኩ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ላበረከተለት የውሃ መሳቢያ ጀነሬተር ትልቅ መነሳሳት የፈጠረለት ሲሆን በቀጣይ በስፋት በማምረት የገበያ ክፍተት ለመሙላት እንደሚሰራ ተናግሯል።

ወይዘሮ አይናለም ረጋሳ እና አቶ ኃይለገብርኤል አባተ በወረዳው የቱባና ተሊሎ አርሶአደሮች ሲሆኑ በበጋ መስኖ ስንዴ ተሰማርተዋል።

እንደአርሶአደሮቹ ገለፃ የበጋ መስኖ ስንዴ ከመደበኛ መስኖ በበለጠ ከፍተኛ ምርት ያስገኛል ብለዋል።

በ2014 ዓም ለመጀመሪያ ጊዜ ባመረቱት የበጋ መስኖ ስንዴ 36 ኩንታል ምርት በሄክታር ማግኘታቸው ዘንድሮ ደግሞ በስፋት እንዱያመርቱ አስችሏቸዋል።

በመሆኑም አርሶአደሮች በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ውሀገብ በሆኑ አካባቢዎች ተደራጅተው በመስራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *