ሴቶች በልማት ህብረት በማደራጀት ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት መምሪያ አስታወቀ።

የሴቶች ልማት ህብረት ለማጠናከር ያለመ የንቅናቄ መድረክ ሴቶችና ህጻናት መምሪያ ከዞኑ ከጤና መምሪያ ጋር በመተባበር በወልቂጤ ከተማ አካሂደዋል።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ሴቶች በዞኑ በሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ እንስቃሴዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆናቸው የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ ሚናቸው የጎላ ነው።

ከዚህ ቀደም ሴቶች በልማት ቡድን ተደራጅተው ጠንካራ የልማት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበርና አሁን ላይ መቀዛቀዝ እንደሚስተዋልባቸው የጠቆሙት አቶ አለማየሁ በቀጣይ በዞኑ የሚገኙ ሴቶች በልማት ህብረት በማደራጀት የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማጠናከር ስራ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ነጅሚያ መሀመድ በንቅናቄ መድረኩ ላይ እዳሉት በዞኑ 154 ሺህ 187 ሴቶች በ4 ሺህ 691 የልማት ቡድን ተደራጅተው ባደረጉት ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የቁጠባ ባህላቸውንና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ከማሳደጋቸውም በተጨማሪ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን እንዲቀንሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በዚህም 96 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠብ መቻላቸውን የተናገሩት ኃላፊዋ ከዚህ ቀደም የሴቶች የልማት ቡድን በመባል የሚጠራው አደረጃጀት የሴቶች የልማት ህብረት በሚል የስያሜ ለውጥ በማድረግ በአዲስ ለማደራጀት የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ እስከ ቀበሌ ድረስ ሊካሄድ ይገባል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በበኩላቸው የሴቶች የልማት ህብረት እንደ አዲስ በማደራጀት በጤናው ሴክተር የተጣሉ ግቦች ለማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች ህብረተሰቡ በማሳተፍ ርብርብ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡

በዞኑ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የጤና ኤክስቴሽን አገልግሎት አሰጣጥ በማነቃቃት በጤና ኬላ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለማዘመን ህብረተሰቡ በማሳተፍ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በየአካባቢያቸው የሚከናወኑ ማንኛውም የልማት እንቅስቃሴዎች ያለ ሴቶች ተሳትፎ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ገልጸው ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች በልማት ህብረት በአዲስ መልኩ በማደራጀት በልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *