ሰኔ21/2015 ዓ.ም

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ለመላው የእስልምና እምነት ተታዮች እንኳን ለ1444ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢድ አል አደሃ አረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ2015 ዓ.ም የኢድ አል አደሃ አረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሀገራችን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖትና ቋንቋ ሳይለያቸው የሚኖሩባት፤ ህዝቦቿ ተቻችለው፣ ተከባብረውና ተረዳድተው በአንድነት ለረጅም ዘመናት በመኖር የዳበረ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ዛሬም ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ባለፉት አምስት አመታት በሀገሪቱ የተፈጠረው ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም መደፍረስ፣ የህግ የበላይነት አለመከበር፣ ህገ-ወጥ ተግባራት የሚፈጽሙ ግለሰቦች መበራከትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በለውጥ ጉዟችን ላይ የገጠሙን ተግዳሮቶች ቢሆኑም ሰላም ወዳዱ ህዝባችን የአንድነትና የአብሮነት አሴቶቹ ሳይሸረሸሩ ተጠብቀው እንዲቆዩ እያደረገ ይገኛል፡፡

በሀገራችን እየተስተዋሉ ያሉ የፀረ ሰላምና የጠላት ኃይሎች ጥፋት ለመመከት እና የሀገሪቱን ሰላምና እንድነትን ለመጠበቅ መንግስት እየሰራ ያለውን ስራ ዉጤታማ ለማድረግ መላው ህዝበ ሙስሊም ከሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖች ጋር በመሆን የበኩላቸውን ማገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የሀይማኖት ተቋማት በሀገር ሰላምና ልማት ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡን በማስተማርና በማነፅ የሚያደርጉት ጥረትም አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የእስልምና እምነት አስተምህሮ እንደሚያስረዳው ወንድማማችነት የሰብዓዊነት እና የዘመናዊነት መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር ርህራሄን፣ ወገናዊነትን፣ መተሳሰብንና መተማመንን እንዲሁም መተዋወቅንና መቀራረብን በውስጡ የያዘ ሀይማኖታዊ እሴት ነው። መተሳሰብ ደግሞ በደስታና በሀዘን ወይም በችግርና በምቾት ጊዜ መደጋገፍን ያሳያል።

ይህ በእስልምና አስተምሮትም ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውና በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ለዘመናት ሲተገበር የኖረ እሴታችን ነው።

ባለንበት ዘመንም ይህንን እሴት ጠብቀን እየኖርን መሆናችን ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የብዙ እምነቶች፣ ማንነቶች፣ ባህሎችና እሴቶች መገኛ ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ይህንን ልዩነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር ናት።

የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉን ስታከብሩ የቀደመ የአብሮነት እሴቶቻችሁን በመጠበቅና እንደ ሀገር በተለይም ባለፉት ዓመታት የደበዘዘውን የወንድማማችነት እሴት እንዲያሰራራ በሚደረገው ጥረት የራሳችሁን አሻራ በማሳረፍ እና የተቸገሩ ወገኖችን፣ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

በድጋሚ እንኳን ለዒድ አል አደሃ አረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ !!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *