ሰኔ 27/2015 በጉራጌ ዞን በ206 የፈተና ጣቢያዎች ሲሰጥ የነበረው ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና በሰላም መጠናቀቁ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

ሰኔ 27/2015
በጉራጌ ዞን በ206 የፈተና ጣቢያዎች ሲሰጥ የነበረው ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና በሰላም መጠናቀቁ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በዞኑ በ2015 ዓ.ም ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና መቀመጣቸው ተጠቁሟል፡፡

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ የ2015 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ተፈታኞች በራሳቸው አቅም መስራት እንዲችሉ ከኩረጃ ነፃ ለማድረግ የተሰራው ስራ አበረታች እንደነበር ገልፀዋል፡፡

የፈተና አስተዳደር ስርዓቱ እና አሰጣጥ ሂደቱ ከወትሮ በተለየ መልኩ ተማሪዎች ከተማሩበት ትምህርት ቤት ውጭ በ206 የፈተና መስጫ ክላስተሮች እንዲፈተኑ የተደረገ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እንዲፈትኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ ተማሪዎች በሌሎች ተማሪዎች ጥገኛ ሳይሆኑ በራሳቸው ጥረት በመፈተን ችሎታቸው እንዲመዝኑ ያስችላቸዋል፡፡

የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ የፈተና አስተዳደር ቁጥጥር ስራ በመሆኑ ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል የፈተና አሰጣጥ ሂደት ከኩረጃ የፀዳ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል አቶ አስከብር ፡፡

በዞኑ በ206 የፈተና መስጫ ክላስተሮች ሲሰጥ የነበረው ክልል አቀፍ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን የገለፁት አቶ አስከብር ለፀጥታ አካላት፣ ለወላጆች እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸው አቅርበዋል፡፡

ተማሪዎች በታችኛው የትምህርት ደረጃ በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ኃላፊው ትምህርት ቤቶች በግብዓት ለማሟላት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ የፈተና አስተዳደርና ቁጥጥር አስተባባሪ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም በበኩላቸው በ2015 ዓ.ም ከ32 ሺህ በላይ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ለክልል አቀፍ ፈተና የተቀመጡ ሲሆን ተማሪዎቹ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲፈተኑ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ከኩረጃ የፀዳ በመሆኑ በቀጣይ በዞኑ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ኩረጃን የሚፀየፉ ተማሪዎች ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

አክለውም አቶ መብራቴ ከሰኔ 28/2015 ጀምሮ የሚሰጠው ዞን አቀፍ የ6ኛ ክፍል ፈተና ከኩረጃ የፀዳ ለማድረግ ተማሪዎቹ በ212 ክላስተሮች እንዲፈተኑ የሚደረግ ሲሆን ፈተናው በሰላም እንዲፀናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸው ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

አንዳንድ ያነጋገርናቸው የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች እንደተናገሩት የፈተና አሰጣጥ ስርዓቱ በራስ የመተማመን ችሎታቸው አሳድጎላቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አስቀድሞ ዝግጅት ያደረጉ ሲሆን ያለምንም ሁከት በስርዓት መፈተን እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ብቁ፣ በራሱ የሚተማመንና በሀገር አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ተግተው እንደሚሰሩ ተማሪዎቹ አስረድተዋል።

ተማሪዎቹ ከፈተና በኋላ ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የተከሉ ሲሆን ቀጣይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች ለማገዝ የደንብ ልብሳቸው አበርክተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *