ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሁሉም ሰው ሊጠብቀው እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ገለጹ።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሁሉም ሰው ሊጠብቀው እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ገለጹ።

በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ከዳርጌ ከተማና በአጎራባች ቀበሌዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ወቅት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተመስገን ካሳ እንደገለጹት ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሁላችንም ልንጠብቀው እንደሚገባና ከእጃችን ከወጣ በቀላል ልናገኘው የማንችለው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

የክልሉ መንግስት የሰላም ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በየደረጃው ከህዝቡ ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ለህብረተሰቡ ስጋት በሚሆኑ አካላት ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

በአበሽጌ ወረዳ ዳርጌ ከተማና አካባቢው ላይ ያለው የሰላም ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመሆን እያሳየው ያለው ቁርጠኝነት አድንቀው አካባቢውን የሚያውኩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና እጃቸውን ለመንግስት በመስጠት ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ክልሉ ከኦሮሚያ በሚዋሰኑ አካባቢዎች ላይ ሰላም እንዲሰፍን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በመሆን ውይይቶች በማካሄድ ላይ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በየትኛውም አደረጃጀትና እንቅስቃሴ ከመንግስት አካላት ጋር በመሆን ሰላም የሚያውኩ አካላትን አሳልፎ መስጠት እንዳለበት የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መመምሪያ ሀላፊ አቶ የህያ ሱልጣን ጠይቀዋል።

በዞኑ ሰላም ለማስፈን በተለያዩ ጊዜያት መድረኮች ተፈጥረው ከህዝቡ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ የህያ የህዝቡን ሰላማዊ ኑሮን የሚያውኩ አካላት ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ለማድረስ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ጠላታችን ድህነት መሆኑን ተገንዝበን በልማት ስራዎች ላይ በማተኮር ለግል አላማቸው ሲሉ በእኩይ ተግባር የተሰማሩ አካላት መንገድ አለመከተል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጁሀር በበኩላቸው የወረዳው ህዝብ ፍላጎት በሰላም መኖርና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብአት ጥያቄ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ወረዳው የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ተዋዶና ተፋቅሮ የሚኖረውን ህዝብ የሚያውኩ አካላት መኖራቸውን ገልጸው ምርትና ምርታማነት የሚረጋገጠው ሰላም ሲሰፍን በመሆኑ በዳርጌ መዘጋጃና አካባቢው እየተስተዋለ ያለው የጸጥታ ችግር በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በአካባቢው ለረጅም ጊዜ ተቻችሎ በኖረ ህዝብ መሀል ላይ የሰላም ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት ማህበረሰቡ ውስጥ ተሸሽገው ያሉ በመሆናቸው ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የመደረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለአካባቢያቸው ሰላም ዘብ እንደሚቆሙና ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላት አሳልፈው ለህግ አካላት በመስጠትና ልጆቻቸውንም ጭምር ሰላምን በሚያውኩና የህብረተሰቡን አብሮነት በሚሸረሽሩ ጉዳዮች ላይ እንዳይሳተፉ በመምከር በልማት ስራዎቻቸው ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸዋል።

መንግስትም በአካባቢው ህግ ማስከበር እንዳለበት ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *